ከነ ህመም ስሜቱ እስከመጨረሻው የተጫወተው የዋልያዎቹ ተከላካይ…

በትናንትናው የኢትዮዽያ ድል ከነ ህመም ስሜቱ እስከ መጨረሻው የተጫወተው የኃላው ደጀን ያሬድ ባዬ ስላለበት ሁኔታ ጠይቀን ያገኘነውን መረጃ እናጋራችሁ።

በተከታታይ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዋች ኢትዮጵያ ምንም ጎል አለማስተናገዷ የመከላከል አደረጃጀቱ እንደ አንድ ጥንካሬ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀስ ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ ከአስቻለው ታመነ ጋር ጥሩ ጥምረት የፈጠረው እና በዘንድሮ ዓመት በሁሉም ጨዋታዎች በወጥ አቋም መሳተፍ የቻለው የኃላ ደጀኑ ያሬድ ባዬ በትናንቱ ጨዋታ በመጀመርያ አጋማሽ ጉዳት አስተናግዶ በህክምና ድጋፍ በፍጥነት ዳግም ወደ ሜዳ በመመለሱን ተመልክተናል። ያሬድ እሰከ ጨዋታው መጠናቀቅ ድረስ ከህመም ስሜቱ ጋር እየታገለ የመከላከል ስራውን በአግባቡ ሲወጣም እንደነበረ አስተውለናል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ያሬድ እግሩ ላይ የህመመም ስሜት እንደነበረው ብሔራዊ ቡድኑ ባረፉበት ብሉ ናይል ሆቴል በተገኘንበት ወቅት መታዘብ ችለናል።

ታዲያ ይህ የህመም ስሜት ምንድነው ብለን ያሬድን ስለ ሁኔታው ጠይቀነው ” ትንሽ የህመም ስሜት አለው። ሆኖም ብዙም አሳሳቢ አይደለም። በተለያዩ እንክብካቤዎች የህመም ስሜቱ የሚጠፋ ነው።” ሲል ገልፆልናል። በተመሳሳይ የህክምና ባለሙያውም ለጠየቅነው ጥያቄ ብዙም አስጊ እንዳልሆነ እና የህመም ስሜቱ በበረዶ በመታሸት የሚጠፋ መሆኑን ገልፆልናል።

ኢትዮጵያ ዳግም ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ወሳኙን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋን የፊታችን ማክሰኞ አቢጃን ላይ ከአይቮሪኮስት ጋር የምትጫወት ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ