ዋልያዎቹ ወደ አቢጃን ጉዞ ጀምረዋል

ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ለወሳኙ ፍልሚያ ጉዞ ይዘዋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ይገኛል። በምድብ 11 ከኮትዲቯር፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር የተደለደለው ቡድኑ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታውን ከኮትዲቯር ጋር ለማከናወን ጉዞ ጀምሯል።

ከትናንት በስትያ ማዳጋስካርን በባህር ዳር ጋብዞ አራት ለምንም የረታው ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት አመሻሽ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል። ወደ አቢጃን ለመጓዝም ልዑካኑ ቁርሱን ባረፈበት ሆቴል ከተመገበ በኋላ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አምርቷል። ከሠላሳ በላይ የሚሆነው የቡድኑ ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለጉዞ የሚያስፈልገውን ቅድመ ፍተሻም አከናውኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ በሥፍራው እንደተመለከተችው ከሆነ በማዳጋስካሩ ጨዋታ በቋሚነትም ሆነ በተጠባባቂነት ያልነበሩት ወንድሜነህ ደረጄ እና ፍሬው ጌታሁን ወደ አቢጃን ከሚጓዘው ስብስብ ውጪ ሆነዋል። ከሁለቱ ተጫዋቾች ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠናል።

በኢትዮጵያን ሰዓት አቆጣጠር 4:30 ከአዲስ አበባ የተነሳው ብሔራዊ ቡድኑን የያዘው አውሮፕላን 9:30 ላይ አቢጃን እንደሚያርፍ ተጠቁሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ