የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ የቴሌቭዥን ሽፋን ጉዳይ

ዛሬ ማምሻውን የሚደረገው ጨዋታ በሱፐር ስፖርት የመተላለፉ ነገር ከምን እንደደረሰ ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ተከታዩን መረጃ አግኝተናል።

የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ከሰዓታት በኋላ በድሬዳዋ ይጀምራሉ። ከከተማዋ ሞቃታማ አየር መነሻነት ጨዋታዎቹ አመሻሽ ላይ እንደሚደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ከቴሌቪዢን ስርጭት ጋር በተያያዘ ያለው ነገር ግን እስካሁን አለየለትም። በስታድየሙ ትናንት ምሽት በነበረው የፓውዛ ገጠማ እና የሙከራ ጊዜ የሱፐር ስፖርት ባለሙያዎች ለምሽት አንድ ሰዓቱ ጨዋታ በቂ ብርሀን ባለማግኘታቸው የዛሬ ሁለተኛ ጨዋታ ሽፋን የማግኘቱ ነገር አጠራጣሪ መዘገባችን ይታወሳል።

ሆኖም ጨዋታውን ለማስተላለፍ አሁንም ጥረቱ ቀጥሎ ተጨማሪ መብራቶችን በመግጠም እና ማስተካከያዎችን በማድረግ ሽፋን ለመስጠት ሙከራው ቀጥሏል። ሱፐር ስፖር በመርሐ ግብሩ ላይ ጨዋታውን እንደሚያስተላልፍ የጠቆመ ቢሆንም ከተቋሙ ኃላፊዎች ለማጣራት እንደሞከርነው የመጨረሻው ውሳኔ የሚታወቀው ሰዓቱ ሲደርስ እንደሆነ መረዳት ችለናል። የተደረጉት ማስተካከያዎች ተፈላጊውን ውጤት ካስገኙ በመጀመሪያው ጨዋታ ማብቂያ ላይ ሙከራዉን አድርገው ቀጣዩን ጨዋታ ስለማስተላለፋቸው የሚያሳውቁ መሆኑንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ