ጅማ አባጅፋር ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በዚህ የዝውውር መስኮት አምስት ተጫዋቾችን አስፈርመው የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾች አክለዋል።

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመሩ በአዳማ ከተማ ዝግጅታቸውን እየሠሩ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች ከነገ በስቲያ ለቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ቀጣይ ፍልሚያ ወደ ድሬዳዋ ያመራሉ፡፡ ቡድኑ ተጠናክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድም የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል፡፡

ዋለልኝ ገብሬ በድጋሚ የቀድሞው ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ወልዋሎ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም የተጫወተበትን ክለብ የተቀላቀለ ሲሆን በአማካይ ክፍል ለአሰልጣኙ አማራጭ እንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል።

ፕሪንስ ሰቨርኒሆ ለክለቡ ፊርማውን ያኖረ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በ2009 ከመጣ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ቡርኪናቤው የመስመር አጥቂ ከአንድ ዓመት የፈረሰኞቹ ቆይታ በኋላ ወደ ወልዋሎ በመጓዝ የሁለት ዓመት ቆይታ አድርጓል። አሁን ደግሞ የቀድሞው አሰልጣኙን በጅማ አባጅፋር ተቀላቅሏል፡፡

ጅማ አባጅፋር በዚህ የዝውውር መስኮት በረከት አማረ፣ ሥዩም ተስፋዬ፣ አማኑኤል ተሾመ፣ አሌክስ አሙዙ እና ራሂም ኦስማኖን ቀደም ብሎ ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ