ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

በሊጉ የእስካሁኑ ቆይታ የመጀመሪያ በሚሆነውን የምሽት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ይህኛው መርሐ ግብር የቴሌቪዢን ስርጭት ያላገኘ ሦስተኛው ጨዋታ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ የጨዋታው ዐብይ ርዕስ የሆነ ይመስላል። ከድሬዳዋ ስታድየም የፓውዛ ሁኔታ ጋር የተገናኘው ይህ ጉዳይ ነገ መጨረሻው የሚታይ ሲሆን ጨዋታው ግን ሜዳ ላይ የሁለቱን የረጅም ጊዜ ተፎካካሪዎች መልካም እንቅስቃሴ እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። ከበላያቸው ካለው ፋሲል ከነማ ውጪ በቅርብ ሌላ ሽንፈት ያላዩት ቡናዎች በፉክክሩ ለመቀጠል ሌላ ነጥብ መጣል አይኖርባቸውም። ሀዋሳ ከተማም ራሱን ለታችኛው ትንቅንቅ ላለማቅረብ ውጤቱ አስፈላጊው ነው።

ከአራት ቀናት በፊት ወደ ድሬ የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ዝግጅታቸው በአመዛኙ በኳስ ምስረታቸው ወቅት ከተጋጣሚ በሚመጣው ግብረመልስ መነሻነት የሚበላሸባቸውን ኳሶች እና ስህተቶች መቀነስ ላይ አተኩሯል። እርግጥ ነው ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር በሀዋሳ ጠንካራ መከላከል እጅግ ከተፈተነበት ጨዋታ በኋላ የተዘጉ በሮችን በማስከፈት ተሻሽሎ ቢታይም ከስህተቶቹ ዋጋ መክፈሉ ግን አሁንም አብሮት አለ። ነገም ሀዋሳ ከጥልቅ መከላከል ይልቅ ፊት ላይ ጫና መፍጠርን ምርጫው ካደረገ ለቡና አደጋ እንዳይሆን ያሳጋል። ቡድኑ ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኋላ ለሚኖረው ስኬት ግን ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ መልካም ዜና የሆነው ጉዳይ በቅርቡ ከቡና ጋር የአራት ዓመት ውል ያሰረው ታፈሰ ሰለሞን ወደ ሜዳ መመለስ ነው። ከእርሱ በተጨማሪም የዊልያም ሰለሞን እና አቡበከር ናስር አስተዋፅኦም የቡና ማጥቃት ላይ ከፍ ያለ ድርሻ እንደሚኖረው ሲጠበቅ ኃይሌ ገብረትንሳይ በጉዳት የማይኖር ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል።

ሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ውድድሩን በአስከፊ ሁኔታ ጀምሮ ነፍስ መዝራት የጀመረው ቡናን በመርታት ነበር። አሁንም ዳግም የተዳከመው አቋሙን ለማስተካከል በተመሳሳይ ቡናን ያገኛል። ባህር ዳር ላይ አጥጋቢ ውጤት ማሳካት ያልቻለው ሀዋሳ በውድድሩ መሐል ላይ ያሳየውን ድንቅ አቋም መልሶ ማግኘት የግድ ይለዋል። ይህንን ለማድረግም ከውድድሩ ዕረፍት መልስ በነበርው ዝግጅት በተቃራኒ ግብ ፊት ስል ሆኖ ለመገኘት እንዲሁም ግብ ሲቆጠርበት ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያሳየው መነቃቃት ከጨዋታ መነሻ ጀምሮ በማምጣት በሙሉ ትኩረት ለመጫወት ሲዘጋጅ ቆይቷል። በነገው ጨዋታም ቡድኑ በተሻለ የፈጣን ሽግግር ማጥቃት ሁለቱን መስመሮች ተመርኩዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። ይህንን አጨዋወት ለመተግበርም መሀል ሜዳ ላይ ወሳኝ ሚና የነበረው ኤፍሬም ዘካርያስ ከጉዳት መመለስ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህርት መልካም ዜና ሆኗል። በአንፃሩ የመስፍን ታፈሰ ጉዳት ላይ መሆን የሀዋሳን የፊት መስመር አስፈሪነት እንዳይቀንስበት ያሰጋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በሊጉ የሁሉም ዓመታት ተሳትፎ ሪከርድ ያላቸው ሁለቱ ክለቦች ነገ ለ44ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። እስካሁን 16 ጊዜ ነጥብ የተጋሩት ቡና እና ሀዋሳ በቀሪዎቹ ሲሸናነፉ ቡና 14 ሀዋሳ ደግሞ 13 ጊዜ ድል አድርገዋል።

– በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የበላይ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 44 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

እያሱ ታምሩ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አቤል ከበደ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ– ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ኤፍሬም ዘካሪያስ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ዮሐንስ ሴጌቦ


© ሶከር ኢትዮጵያ