የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስተኛ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ፡ አዳማ ከተማ አሸንፏል። አርባምንጭ ከተማም ከሊጉ መውረዱ ተረጋግጧል፡፡
10፡00 ላይ በሊጉ ለመቆየት ማሸነፍ አልያም አቻ መውጣት የሚጠበቅበት አዳማ ከተማ እና አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አገናኝቷል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በተመለከትንበት ጨዋታ ነጥቡ ያስፈልገው የነበረው አዳማ ከተማ በተሻጋሪ ኳስ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከረበት እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እንደተለመደው ወደ መስመር በማጋደል በመጫወት ዮርዳኖስ ምዑዝን ለመጠቀም ሞክረዋል።
በዚህ የመስመር አጨዋወት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ሙከራን አድርገዋል፡፡ በቀኝ በኩል የአዳማዋ አምበል ናርዶስ ጌትነት የያዘችውን ኳስ ዮርዳኖስ ምዑዝ በፍጥነት ነጥቃት ወደ ግራ በኩል ለፍሬወይኒ ገብረፃድቅ ስጥታት ተጫዋቿ ነፃ ቦታ ላይ ለነበረችው ሣራ ነብሶ አቀብላት አጥቂዋ አክርራ ስትመታው እምወድሽ ይርጋሸዋ አድናባታለች፡፡ በአዳማ በኩል 25ኛው ደቂቃ ብሩክታዊት አየለ ከመስመር አሻምታ ምስር ከግቡ ትይዩ ጋር ሆና ወደ ጎል በቀጥታ ስትመታው ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በግሩም ሁኔታ መልሳባታለች፡፡
ከእረፍት ሲመለሱ አራት ያህል ደቂቃ እንደተቆጠረ ከመሀል ሜዳ ፀባኦት መሐመድ በረጅሙ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል በምታሳልፍበት ወቅት የኤሌክትሪኳ ተከላካይ ዘለቃ አሰፋ ኳሷን በአግባቡ ለመቆጣጠር ጥረት ባለማድረጓ የምስራች ላቀው ፍጥነቷን በመጠቀም ያገኘቻትን ኳስ ወደ ጎል በመለወጥ አዳማን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ጎል ካስተናገዱ በኋላ በዮርዳኖስ ምዑዝ እና ሣራ ነብሶ አማካኝነት የማግባት ዕድሎችን ለማግኘት ኤሌክትሪኮች ጥረት ቢታይባቸው ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ሲደርሱ በነበራቸው ዝንጉነት ሊያመክኑ ግድ ብሏቸዋል። አዳማዎችም 78ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎላቸውን በምስራች ላቀው አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው 2ለ0 ተደምድሟል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ የመውረድ አደጋ የነበረበት አዳማ በፕሪምየር ሊጉ መቆየቱን ሲያረጋግጥ በአንፃሩ ዛሬ ጠዋት አቃቂን አሸንፎ የነበረው አርባምንጭ ከተማ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረዱን አረጋግጧል፡፡
ነገ የመጨረሻ እና የዋንጫ ስነ ስርአት በሚደረግበት ዕለት ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ ጠዋት 3፡00 መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ፤ 5፡00 ቻምፒዮኑ ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከተማን ይገጥማሉ።
© ሶከር ኢትዮጵያ