የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቻምፒዮንነት ፍፃሜውን አግኝቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ ስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ውድድሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 2ለ0 ሲረታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ አበባን በማሸነፍ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ አንስቷል፡፡

3፡00 ሲል ቀደም ብለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው መርሐ ግብር የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ነበሬ፡፡ ጠንካራ ፉክክርን ባየንበት እና የሀዋሳ ከተማዎች ጥሩ አጀማመር በነበረበት ጨዋታ ገና በጊዜ ነበር ጎል መመልከት የቻልነው። ካሰች ፍሰሀ ከግራ ወደ መከላከያ የግብ ክልል በረጅሙ የላከችውን ኳስ ረድኤት አስረሳኸኝ በአግባቡ ተቆጣጥራ ወደ ግብነት በመለወጥ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች ቀስ በቀስ እየወረዱ ሲመጡ በአንፃሩ መከላከያዎች አቻ ለመሆን ታትረዋል፡፡በተለይ መሳይ ተመስገን እና ሴናፍ ዋቁማ የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር አስፈሪ በሆነ እንቅስቃሴ ታጅበው ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ጠንካራውን የሀዋሳ ተከላካይ ለማለፍ እጅጉን ከብዷቸው በአጋማሹ ታይቷል፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻሉ ቢሆኑም የሀዋሳ ከተማ የአጨራረስ አቅምን በደንብ ማስተዋል የቻልንበት ነበር፡፡ 52ኛው ደቂቃ ላይ ዙፋን ደፈርሻ መሐል ለመሐል የመከላከያን የተከላካይ ክፍተት ተመልክታ የላከችላትን ኳስ መሳይ ተመስገን በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጣ የሀዋሳን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡ ከሦስት ደቂቃዎች በኃላ መሳይ ከታሪኳ በርገና ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ሌላ ጎል አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡

የቀሩትን ደቂቃዎች ኳስን በማንሸራሸር ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል መከላከያዎች በተደጋጋሚ መድረስ ቢችሉም ተከላካዮችን አልፈው ጎል ለማግኘት ግን አልቻሉም፡፡ 57ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያዋ የግራ መስመር ተከላካይ ነፃነት ፀጋዬ በዙፋን ደፈርሻ ላይ በሰራችው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች። ተጫዋቿም በእንባ ታጅባ ሜዳውን ለቃ ወጥታለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ሀዋሳ ከተማ 2ለ0 በማሸነፍ ዓመቱን በድል ዘግቷል፡፡

በመቀጠል ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዲስ አበባ ከተማ የመጨረሻ ጨዋታውን ተፈትኖም ቢሆን በድል ተወጥቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የአዲስ አበባ ከተማ የእንቅስቃሴ እና የሙከራ ብልጫን የተመለከትን ሲሆን 28ኛው ደቂቃ ላይ ታሪኳ ዴቢሶ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ በግብ ክልላቸው አካባቢ የተሰጠውን የቅጣት ምት ቤተልሄም ታምሩ አስቆጥራ አዲስ አበባን መሪ አድርጋለች፡፡

ባንኮች በዚህ አጋማሽ ሎዛ አበራ እና ከቅጣት ምት ዓለምነሽ ገረመው ካደረጓቸውት ሙከራዎች ውጪ የጠሩ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በአጥቂዎች መረጋጋት አለመቻል ምክንያት ተጨማሪ ግብን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

ከእረፍት መልስ ንግድ ባንኮች አረጋሽ ካልሳን በፎዚያ መሐመድ ተክተው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኃላ ጎል ለማግኘት የፈጀባቸው አምስት ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ አረጋሽ ካልሳ በመጀመሪያ ንክኪዋ ለሰናይት ሰጥታት አማካይዋ አክርራ መትታ የግቡ ብረት ሲመልስው በቅርብ ርቀት ላይ የነበረችው ሎዛ አበራ አስቆጥራው ክለቧን አቻ አድርጋለች፡፡ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ሎዛ አበራ እጅግ አስገራሚ የቅጣት ምት ጎል አስቆጥራ ክለቧን 2ለ1 አሸናፊ አድርጋለች፡፡ አጥቂዋ በዛሬው ዕለት ሁለት ጎሎችን በማስቆጠሯ የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆናም ጨርሳለች፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የመዝጊያ ስነ ስርአት ተከናውኗል፡፡ በክብር እንግድነት የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና ኮሚሽነሩ አማካሪ አቶ መንግሥቱ ሳህሌ፣ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ የፌዴሬሽኑ ምክትል ዋና ፀሀፊ፣ እንዲሁም አቶ አቤ ሳኖ የንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ የበላይ ጠባቂ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው የተዘጋጁትን ሽልማቶች አበርክተዋል፡፡በቅድሚያ ለውድድሩ ድምቀት የሰጡ አካላት እና ተቋማት ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ውድድሩን ከጅምር እስከ ፍፃሜውን ለህብረተሰቡ በማድረሷ የምስክር ወረቀት ዕውቅና ተሰጥቷታል። የአርባምንጭ ከተማ የሴቶች ክለብ ጉዳት በገጠመን ወቅት ከጎናችን ለነበሩት ክለቦች እና ግለሰቦች እናመሰግናለን በማለትም ምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡ ልሳን የሴቶች ስፖርት ደግሞ ለውድድሩ መሳካት ለተጉ ሰዎች የራሳቸውን ምስል የያዘ ስጦታም አድርሷል፡፡

በመቀጠል በእለቱ ክብር እንግዳ አቶ መንግስቱ አማካኝነት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የነሀስ ሜዳሊያ፣ መከላከያ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ የብር ሜዳሊያ ሽልማትን ሲያገኝ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወርቅ እና የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ተሸልሟል፡፡

በመጨረሻም የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና የአመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ፣ ረሂማ ዘርጋው ከንግድ ባንክ በምርጥ ተጫዋችነት፣ ሎዛ አበራ በበኩሏ በ17 ጎሎች በምርጥ ጎል አስቆጣሪነት ፣ ንግድ ባንክን ቻምፒዮን ያደረገው ብርሀኑ ግዛው በምርጥ አሰልጣኝነት መመረጥ ሲችሉ በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር ላይ በአንድ ሆቴል በሚዘጋጅ ፕሮግራም ሽማታቸውን የሚወስዱ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ክለብ በ9.34 አማካይ ነጥብ የውድድሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ እና አዳማ ከተማ ደግሞ በአስተናጋጅነት የተዘጋጀላቸውን ዋንጫ ከተሸለሙ በኃላ ውድድሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ