በርካታ ተጫዋቾችን ያፈራው ወጣት ቡድን ተበተነ

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነው የወላይታ ድቻ ቡድን ከውድድር ውጪ መሆኑ ታውቋል፡፡

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የምድብ ሀ ተሳታፊ በመሆን አሰላ ላይ በመጀመሪያው ዙር በሰበሰው 12 ነጥብ በመሪነት ያጠናቀቀው ይህ ቡድን በአዳማ ለሚደረገው የሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች በበጀት ምክንያት እንዳይሄድ በክለቡ አመራሮች በመገለፁ መበተኑን የቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ሎሀ እና ተጫዋቾቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። “ለሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ ሆኖ ለመቅረብ ስንዘጋጅ ነበር። አሁን ግን በክለቡ አመራሮች አትሄዱም ስንባል ልፋታችን ገደል የገባ ያህል ተሰምቶናል። አቤት የምንለው እና ትኩረት የሚሰጠን ባለለመኖሩ ወደየመጣንበት ተበትነናል በማለት።” ገልፀውልናል፡፡

ይህ ጉዳይ ከምን መነሻነት ነው ሊፈፀም የቻለው በማለት ለክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ኃይሌ በተደጋጋሚ ጥያቄ ለማቅረብ ብንደውልም ስልክ ለማንሳት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ለወላይታ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት ኃላፊ አቶ አቦዬ ገካ ጥያቄ አቅርበን በዋናነት ቡድኑ በበጀት እጥረት የተነሳ እንደማይጓዝ አረጋግጠውልናል፡፡ “ክለቡን እንደግፋለን የሚሉ በቃል ደረጃ ሞልተዋል። ‘ደም ሰጥቼ ክለቡን እደግፋለሁ’ ይላሉ። መቶ ብር የሚሰጥ ግን የለም። እንደ መንግሥት አራት አምስት ክለብ ይዘናል። አሁን ባለው ወቅታዊ ችግር ደግሞ የገንዘብ እጥረት አለ። ይሄ ደግሞ ሀገራዊም ክልላዊም ችግር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ይሄ የሆነው። መጀመሪያም ቡድኑ ሲቋቋም ማንም ፈልጎ ሳይሆን መንግሥት ፈልጎ ነው ያቋቋመው። ትልቁን ቡድን ቢሆን ለዚህ አድርሰን ወጪ አውጥተን ለዚህም ቡድን ወደ ውድድር እንዲገቡ ያደረገው ዞኑ ነው፡፡ በክፋት ወይም ባለመፈለግ አይደለም። ለምን አልተወዳደርንም ብለዋል። ይሄ ደግሞ የተወዳዳሪ ባህሪ ነው እነሱ ተልዕኮአቸውም መወዳደር ነው፡፡ የበጀት ችግሩ ስለመጣ ግን በዚህ ውድድር ላይ እንዳይካፈሉ ሆኗል፡፡” ሲሉ ገልፀውልናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ