የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች መካሄድ ቀጥለው ዛሬ በሦስቱ ምድቦች ሰባት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

በምድብ ሀ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪ የሆነበትን ጣፋጭ ድል አግኝቷል፡፡ 3፡00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን ገና ከጅምሩ ነበር ጎል ማስቆጠር የቻሉት። 9ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የፋሲል ከነማ እና ጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኤርሚያስ ኃይሉ ከማዕዘን የተገኘን ኳስ በፍጥነት ወደ ጎል ክልል መሬት ለመሬት ሲያሳልፍ አማካዩ እንዳለ ዘውገ የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ግብ ጠባቂ ሙሴ ገብረኪዳን የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ኤሌክትሪክ መሪ የሆነበትን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ከጎሉ በኋላ ተጨማሪ ጎሎችን ለማግኘት በሁለቱም መስመሮች ሲፈነጩ የዋሉት የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ተጫዋቾች በርካታ አጋጣሚን መፍጠር ቢችሉም የአጨራረስ ክፍተታቸው ግን በግልፅ ታይቷል፡፡ በተለይ 16ኛው ደቂቃ በግራ የደብረብርሃን የግብ ክልል አካባቢ አቅሌሲያስ ግርማ አክርሮ መቶ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት፣ 25ኛው ደቂቃ አቅሌሲያስ በተሰለፈበት የግራ መስመር ወደ ጎል ከመስመሩ ጠርዝ ሲያሻማ የተሻ ግዛው በግንባር ገጭቶ በሚያስቆጭ ሁኔታ ያመከነበት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን አብዛኛዎቹን የጨዋታ መንገድ ወደ ኃላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የተወሰነ ጥረት ለማድረግ ቢችሉም ወጥነት የጎደለው የቅብብል ሂደታቸው ውጤታማ አላደረጋቸውም፡፡

ብዙም የግብ ሙከራን ባላየንበት እና በመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የነበሩት ደብረብርሃኖች ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሞከሩበት፤ ኤሌክትሪኮች በአንፃሩ ወደ ጎል በመድረስ ባይታሙም በሚገባ በተጋጣሚያቸው የተፈተኑበት ነበር፡፡ ሙሉቀን ወንድሙ ከቅጣት ምት ከርቀት መትቶ ዘሪሁን ታደለ ከያዘበት ኳስ ውጪ ደብረብርሃኖች በእንቅስቃሴ ካልሆነ በሙከራ ስክታማ አልነበሩም። በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ጓል እየመሩ የሚገኙት ኤሌክትሪኮች በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከዚህ በፊት የተጫወቱት ፀጋ ደርቤ እና አደም አባስን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ይበልጥ ቡድኑ ላይ መነቃቃት የታየ ቢመስልም ጎል ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው 1ለ0 ተጠናቋል፡፡ ኤሌክትሪክም ነገ መከላከያ እስኪጫወት ድረስ ምድቡን በሶስት ነጥብ ልዩነት መምራት ጀምሯል፡፡

የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ 10፡00 ሰአት ሲል በገላን ከተማ እና ፌዴራል ፖሊስ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ በትላንትናው ዕለት ህይወቱ ላለፈው ፌድራል ዳኛ ዳንኤል ግርማ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ ነበር የጀመረው፡፡ ብዙም ሳቢነት ባልነበረው እና ሊያጓጓ ሚችል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማየት ባልቻልንበት ሁለቱም አጋማሾች በተወሰነ ረገድ ገላን ከተማ አልፎ አልፎ ጎሎችን ለማግኘት ከሚፈጥሩት ዕድሎች ውጪ በወጥነት ሊገለፁ የሚችሉ ሙከራዎች ሲያደርጉ አልተመለከትንም። ከማል አቶም በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለተኛው አጋማሽ፤ ተቀይሮ የገባው ኪቲካ ጅማ ደግሞ በግል ጥረቶቻቸው ዕድሎችን ለመፍጠር ከመመጣር ውጪ ሳቢነት ያለውን የጨዋታ ሂደት ሳያስመለክተን ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡

በምድብ ለ መሪው አዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲን 3 ለ 0 በመርታት ተከታታይ ድሉን አሳክቷል። ሮቤል ግርማ በ30ኛው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ ከዕረፍት በኋላ ፍፁም ጥላሁን እና አቡበከር ወንድሙ ተጨማሪ ጎል አክለው የእስማኤል አቡበከር ቡድን አሸንፎ እንዲወጣ አስችለዋል።

የካፋ ቡና እና ቤንችማጂ ቡና ጨዋታ በቤንችማጂ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወንድሜገኝ ኪራ በፍጹም ቅጣት ምት እና በጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች ያስቆጠራቸው ጎሎች ቤንችማጂን ለድል አብቅተዋል። በዚህ ምድብ ሊደረግ የነበረው የሻሸመኔ ከተማ እና ነቀምት ከተማ ጨዋታ በኮቪድ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

በየሳምንቱ ተለዋዋጭ ውጤት ማስመልከቱን በቀጠለው ምድብ ሐ ኢትዮጵያ መድን በሺንሺቾ 2-1 ተሸንፏል። ሺንሺቾዎች በጃፋር ከበደ እና ምንተስኖት ታምሬ ጎሎች መምራት የቻሉ ሲሆን የብርሀኑ ቦጋለ ጎል መድንን ከሽንፈት ልታስቀር አልቻለችም።

የካ ከባቱ ከተማ አንድ አቻ ሲለያዩ ነገሌ አርሲ በፀጋ ታዬ ሁለት እና መሳዮ ወንድሙ አንድ ጎል ደቡብ ፖሊስን 3-1 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ