ሎዛ አበራ ዓመቱን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ስለማጠናቀቋ ትናገራለች

ከወራት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ “ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ አጠናቅቃለሁ” ብላ ተናግራ የነበረችውና በቃሏ መሠረት ይህን ክብር የተጎናፀፈችው ሎዛ አበራ ትናገራለች፡፡

የማልታው ቢርኪርካራን ለቃ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ዘንድሮ የተቀላቀለችው ሎዛ አጀማመሯ ጥሩ ባይሆንም ቀስ በቀስ ወደ ጎል አዳኝነቷ በመመለስ ዛሬ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ፕሪምየር ሊግ ላይ ኮከብ ጎል አግቢ መሆኗን አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጎል ካገባች በኃላ አረጋግጣለች። የአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራት ቆይታ “ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ አጠናቅቃለሁ” ብላ የነበረችው ሎዛ በ17 ጎሎች የ2013 ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ማጠናቀቋን ተከትሎ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ብላለች፡፡

ስለ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቷ

“ከአንተ ጋር በነበረኝ ቆይታ ተናግሬ የነበረውን ዛሬ አሳክቼዋለሁ። ፈጣሪ ለዚህ ክብር ስላበቃኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። በእኔ አቅም ሳይሆን በብዙ ነገሮች ረድቶኛል።”

ስለውድድር ዘመኑ

“ብዙ ጊዜ አዲስ ቡድን ውስጥ ስትመጣ ያለህን ወጥ አቋም ለማስኬድ ይቸግርሀል። ማለትም አዲስ ቡድን ሲሆን ሲስተሙንም የቡድኑንም ሁኔታ ለመላመድ ብዙ ጊዜን ይወስዳል። እና ቀስ በቀስ ግን እየተላመድኩ ራሴንም እያሻሻልኩ፣ ድክመቶቼ ላይ በመሥራት ጥሩ ለመሆን ሞክሪያለሁ። ያንን ማድረግ ስለቻልኩም ክለቤ ንግድ ባንክ ቻምፒዮን ሆኗል። እኔም ደግሞ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ ስለጨረስኩ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። ጌታ የተባረከ ይሁን።”

ከደደቢት፣ ከአዳማ ከተማ እና ከንግድ ባንክ ጋር ዋንጫ ማንሳት የፈጠረባት ስሜት

” በጣም ደስ ብሎኛል። ሁልጊዜ በሄድክበት ሻምፒዮን መሆን የሚኖረው ስሜት ከባድ ነው። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ከጀመርኩ ወዲህ ሁለት ዓመት ብቻ ነው (ሀዋሳ ከተማ) ቻምፒዮን ያልሆንኩት። በሌሎቹ ኮከብ ጎል አግቢ በመሆን ጭምር ዋንጫ አሳክቻለሁ። ለዚህ ደግሞ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ጥሩ ጥምረት ፈጥረን ለመጫወት መሞከራችን እኔን በይበልጥ ጎልቼ እንድወጣ እና ውጤታማ እንድሆን አድርጎኛል፡፡ ቻምፒዮን መሆንም ኮከብ ጎል አግቢ መሆንም ብቻዬን ያመጣሁት አይደለም። ምንም ያህል ጎበዝ ብሆን ብቻዬን የምፈጥረው ነገር የለም። እንደ ቡድን የመጣ ስለሆነ ደስ ብሎኛል። ከሁሉም በላይ ግን ፈጣሪ ከእኔ ጋር ስለነበር የተገኘ ድል ነው፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ