ዋልያው ጨዋታውን ሳይጨርስ ወደ አፍሪካ ዋንጫው አልፏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች በተፈጠሩ ድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈበትን ጣፋጭ ዕድል አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከቀናት በፊት የማዳጋስካር አቻውን በባህር ዳር ካሸነፉበት ቀዳሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ተክለማርያምም ሻንቆ፣ አስራት ቱንጆ፣ ያሬድ ባዬህ፣ አስቻለው ታመነ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ሽመልስ በቀለ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አቡበከር ናስር እና ጌታነህ ከበደን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ የማዕዘን ምት ያገኙት አይቮሪ ኮስቶች አጋጣሚውን በአምበላቸው ሰርጂ ኦሪየ አማካኝነት አሻምተውት የመሐል ተከላካዩ ዊሊ ቦሊ ወደ ግብነት ቀይሮት መሪ ሆነዋል። ገና በጅማሮ ግብ ያስተናገዱት ዋልያዎቹ በ8ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት በሞከረው ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረው ነበር። በተጨማሪም በ17ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ለአቡበከር ናስር ጥሩ ኳስ ባመቻቸለት አጋጣሚ ቡድኑ ወደ ግብ ቀርቦ ነበር።

ገና በጊዜ ግብ ማስቆጠራቸው ተረጋግተው እንዲጫወቱ የጠቀማቸው አይቮሪኮስቶች በ19ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት የሚያሰፉበትን ዕድል በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን ናስር ኤቭራርድ ኩዋሲ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍራንክ ኬሲ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ኳሱን ተቆጣጥረው ቢጫወቱም የአይቮሪኮስት የግብ ክልል ጋር መድረስ የተሳናቸው ዋልያዎቹ ከሳጥን ውጪ የሚያገኟቸውን ኳሶች በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በ36ኛው ደቂቃም ሽመልስ በቀለ ከመሐል ነጥቆ ያቀበለውን ኳስ ጌታነህ ከርቀት ወደ ግብ መትቶት ሲልቪያን ግቦሆ አምክኖታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ጌታነህ ከአስራት ቱንጆ የተቀበለውን ኳስ በተመሳሳይ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት በባለሜዳዎቹ አይቮሪኮስት ሁለት ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ረጃጅሞቹን እና ፈርጣማዎቹን የአይቮሪኮስት ተከላካዮች ማለፍ ተስኗቸው ታይቷል። በተቃራኒው ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ ማከናወን የቀጠሉት አይቮሪኮስቶች በ50ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በዚህም ኤቭራርድ ኩዋሲ ከቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ጎል ልኮት የግቡ አግዳሚ ዕድሉም አምክኖታል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ሱራፌል ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ጌታነህ ወደ ግብ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል።

አልፎ አልፎ ፈጥነት የታከለበት የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲተገብሩ የነበሩት አይቮሪኮስቶች በ66ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህ ደቂቃም ኤቭራርድ ኩዋሲ ለዩሐን ቦሊ ጥሩ ኳስ ከቀኝ መስመር አቀብሎት ረጅሙ አጥቂ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የፊት መስመራቸውን ያጠናከሩት ዋልያዎቹ በ73ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃም ሽመክት ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት በሚገርም መረጋጋት ለአቡበከር አቀብሎት ወደ ጎል የተሞከረውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጌታነህ ከበደ ኳሱን ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ለተቆጠረባቸው ጎል ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ፈጣን ምላሽ የሰጡት ባለሜዳዎቹ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ኤቭራርድ ኩዋሲ የግል ጥረት ታግዘው ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲጥሩ ጎል የተቆጠረባቸው ዋልያዎቹ በ78ኛው ደቂቃ በግቡ ባለቤት ጌታነህ በተመታ የርቀት ኳስ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ነበር። ጨዋታው ቀጥሎም በ82ኛው ደቂቃ ጋናዊው የመሐል ዳኛ ቻርለስ ቡሉ ድንገተኛ ህመም አጋጥሟቸው ጨዋታው ተቋርጧል። የመሐል ዳኛው ያጋጠማቸው ህመም የከፋ መሆኑን ተከትሎም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። ጨዋታውም በዚህ ምክንያት እንዲቋረጥ ሆኗል።

ምንም እንኳን ዋልያው በአይቮሪኮስት ሦስት ለአንድ እየተመራ ጨዋታው ቢቋረጥም በምድቡ ሌላ ጨዋታ ኒጀርን በሜዳዋ ያስተናገደችው ማዳጋስካር ነጥብ መጣሏን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ