የኮትዲቯር እና ኢትዮጵያ ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃዎች…

ጋናዊው የመሐል ዳኛ ቻርለስ ቡሉ ድንገተኛ ህመም ተቋርጦ ዳግም ስለተደረገው ጨዋታ መረጃዎችን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 (በ2022 የሚደረግ) የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን በዛሬው ዕለት ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው በኮትዲቯር ሦስት ለአንድ ቢሸነፍም ማዳጋስካር ኒጀርን ማሸነፍ ባለመቻሏ በተገኘ ዕድል ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን አረጋግጧል።

አቢጃን ላይ እየተደረገ የነበረው የዋልያው እና ዝሆኑ ፍልሚያ 81ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው አልቢትር ቻርለስ ቡሉ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም እንዲቋረጥ ሆኗል። ጋናዊው አርቢትር ጨዋታውን መምራት ያልቻሉት የዕለቱ አየር ከብዷቸው በተፈጠረባቸው ህመም እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ድንገተኛ ህመም ያጋጠማቸው ቻርለስ ወዲያው ወደ ህክምና ቦታ ተወስደው ጨዋታው ከተቋረጠ ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ተከናውኖ ያለውጤት ለውጥ 3-1 ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል:-

– የኮትዲቯር እና የኢትዮጵያ ጨዋታ ሊጀመር 3 ሰዓት ሲቀረው የእለቱ ዋና ዳኛ በኮቪድ መያዛቸውን ተከትሎ የጨዋታው ኮሚሽነር ከካፍ ጋር በመነጋገር 4ኛ ዳኛው ጨዋታውን የመምራት ሚና ሲሰጠው፤ ጨዋታው ያለ 4ኛ ዳኛ እንዲጀመር የጨዋታው አስተባባሪ እና የጨዋታው ኮሚሽነር ወሰኑ።

– ጨዋታው በ31 ዲግሪ ሴሊሽየስ እና humidity 82 የተካሄደ ሲሆን፤ የውሃ እረፍት እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ብንጠይቅም በውድድሩ በካፍ የተመደቡት ዶክተር እምቢታን በመምረጥ ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን 81ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ሲመሩ የነበሩት ዳኛ በነበረው የአየር ሁኔታ ተዝለፍልፈው በመውደቃቸው ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ፤ ጨዋታው ያለ 4ኛ ዳኛ ሲመራ ስለነበር ጨዋታው 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል።

– በመቀጠል ሌላ ኮትዲቯራዊ ረዳት ዳኛ እንዲመጣ ተደርጎ ጨዋታውን የመስመር ዳኛው እዲመሩ የሳቸውን ቦታ ደግሞ ኮትዲቯራዊው ተተክቶ ጨዋታው ከተቋረጠ ከአንድ ሰዓት በኋላ ዘጠኙን ደቂቃ እንድንጫወት ተድርጎ ጨዋታው ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ