ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ምሽት ይገባሉ

በትናንትናው ዕለት ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሳቸውን ያረጋገጡት ዋልያዎቹ አዲስ አበባ የሚደርሱበት ሰዓት ታውቋል።

በኮቪድ ምክንያት ከ2021 ወደ 2022 የተዘዋወረው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አይቮሪኮስትን ተከትሎ ወደ መሠረተው አፍሪካ ዋንጫ ማለፉን በትላንትናው ዕለት አረጋግጧል። ቡድኑ ትላንት ምሽት በድራማዊ ክስተቶች ታጅቦ ተቋርጦ ዳግም የተጀመረው ጨዋታን ካገባደደ በኋላ ባረፈበት ሲን ሆቴል ደስታውን ሲገልፅ ማምሸቱንም ሰምተናል።

ብሔራዊ ቡድኑ ጣፋጩን ዕድል እያጣጣመ ካደረ በኋላም ዛሬ ረፋድ ወደ አዲስ አበባ ለማምራት መሰናዳት ይዟል። ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ባገኘችው መረጃ መሠረት ከደቂቃዎች በፊት ብሔራዊ ቡድኑ የቅድመ ጉዞ ዝግጅቱን ለማከናወን ወደ ኤርፖርት መጓዝ ጀምሯል። በአሁኑ ሰዓትም የቡድኑ ልዑካን በአቢጃን አይር ማረፊያ እንደሚገኝ አረጋግጠናል። ልዑካኑ ለጉዞ የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅ ካከናወነ በኋላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 8 ሰዓት ገደማ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንደሚጀምር አረጋግጠናል። ስብስቡም ለአምስት ሰዓታት የሚቆይ የበረራ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ ምሽት 2 ሰዓት ከሰላሳ ላይ አዲስ አበባ እንደሚገባ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ