የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጀግና አቀባበል ሊደረግለት ነው

ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ዋልያዎቹ ለፈፀሙት ገድል የክብር አቀባበል ሊደረግላቸው መሆኑ ተነግሯል።

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2021 (በ2022 የሚደረግ) የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን በትላንትናው ዕለት ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ስምንት ሰዓት ከአቢጃን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንደሚጀምር ተነግሯል። ብሔራዊ ቡድኑ ለአምስት ሰዓታት ገደማ የአየር በረራን ካከናወነ በኋላ ምሽት ሁለት ሰዓት ከሰላሳ አዲስ አበባ ይገባል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ታላቅ ተጋድሎ አድርጎ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሰውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በማርሽ ባንድ በታጀበ ሁኔታ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት እንደሚያደርግለት ታውቋል። ማርሽ ባንዱም ከአቢጃን የተመለሰውን ልዑክ በጀግና አቀባበል ከተቀበለ በኋላ እስከ ሆቴል ድረስ አጅቦ እንደሚያደርስም ተገልጿል።

ብሔራዊ ቡድኑ አዳሩን በሆቴል ካደረገ በኋላም በተመሳሳይ የስፖርት ኮሚሽን በሚያዘጋጀው ዝግጅት የነገ ውሎውን ያሳልፋል። በዚህም ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው ክፍት አውቶብስ ተጫዋቾቹ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንደሚዘዋወሩ ሰምተናል። ከዚህ መርሐ-ግብር በኋላም ታላላቅ የክብር እንግዶች በተገኙበት የማበረታቻ የሽልማት መርሐ-ግብር እንደሚኖር አረጋግጠናል። ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ