ዕውነታ | ዋልያዎቹ አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል

ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያስመዘገባቸውን አዳዲስ ታሪኮች አጠናክረን ይዘንላችሁ ቀርበናል።

በ1957 የአፍሪካ ዋንጫን የመሰረተችው ኢትዮጵያ መድረኩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ከተሳተፈችበት 2013 በኋላ ዳግም ወደ አህጉሩ ትልቁ የሀገራት ውድድር ተመልሳለች። ብሔራዊ ቡድኑ በ2022 በሚደረገው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከአይቮሪኮስት፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር ተደልድሎ ለረጅም ወራት የዘለቀ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የከረመ ሲሆን በትላንትናው ዕለትም ረጅሙን ሩጫ በመጨረስ አይቮሪኮስትን በመከተል ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን አረጋግጧል። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ታሳቢ በማድረግ በዘንድሮ የማጣሪያ ጨዋታዎች የተመዘገቡ አዳዲስ ዕውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናቸዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ የሆነው ካፍ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች በአዲስ መልክ በምድብ ተከፋፍለው እንዲካሄዱ ያደረገው ከ1992 ጀምሮ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተደረጉ 14 የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአስሩ ላይ ተሳትፎን አድርጓል። ምንም እንኳን ቡድኑ በአስር የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሳታፊ ቢሆንም በአንዱም ማለፍ ሳይቸል ቀርቶ ነበር። ዘንድሮ ግን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን አልፎ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ተሳታፊ የሚሆንበትን ሪከርድ አስመዝግቧል።

ከላይ እንደተገለፀው ዋልያው በአስር የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎን አድርጓል። በአስገራሚ ሁኔታም ብሔራዊ ቡድኑ በተሳተፈባቸው ሁሉም የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የግብ እዳን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። 1994 በ12፣ 1994 በ5፣ 1996 በ14፣ 1998 በ16፣ 2004 በ2፣ 2008 በ4፣ 2012 እና 2015 በ5 እንዲሁም 2017 በ3 በ2019 ደግሞ በ10 የግብ እዳ የምድብ ጨዋታዎችን አገባዷል። ዘንድሮ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ግብ እዳ በአራት የግብ ክፍያ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ጨርሷል።

ብሔራዊ ቡድኑ በአሁኑ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ያስመዘገበው አዲስ ታሪክ ከነጥብ ጋር የተገናኘ ነው። ቡድኑም ትናንት ባጠናቀቀው የማጣሪያ ጨዋታ ዘጠኝ ነጥቦችን ሰብስቧል። ይህም ብሔራዊ ቡድኑ በአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቀጥሎም በገብረመድኅን ኃይሌ እየተመራ 2017 ላይ ከሰበሰበው 11 ነጥቦች በኋላ በርከት ያሉ ነጥቦች የተሰበሰበበት ሆኖ ተመዝግቧል። በአጠቃላይ ከነበሩት የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ሆኗል። በዚህም የዘንድሮ ማጣሪያ ውጤት 2004 ላይ ከተመዘገበው ጋር የተስተካከለ ሆኗል። እንደተገለፀው ቡድኑ 2004 ላይ 9 ነጥቦችን ቢሰበስብም በምድቡ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ ሳይችል ቀርቶ እንደነበር ይታወሳል።

የመጨረሻው አዲስ ታሪክ ደግሞ ግቦችን ከማስተናገድ ጋር የተያያዘ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች በታሪኩ ዝቅተኛ ጎሎችን ያስተናገደው ዘንድሮ ነው። ቡድኑም በምድብ አስራ አንድ ተደልድሎ ባከናወናቸው ስድስት ጨዋታዎች ያስተናገዳቸው ጎሎች ብዛት ስድስት ብቻ ናቸው። ይህም በምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ታሪክ ዝቅተኛ ጎሎች ያስተናገደበት ሆኖ ተመዝግቧል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነበሩት የማጣርያ ጨዋታዎች ይመዘገብበት ከነበረው በጨዋታ 2.25 ጎል በጨዋታ አንድ ጎል ወርዷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ