“…እኛ እንደውም የቀረውን ደቂቃ ረስተን ወደ መጨፈሩ ነበር ያመራነው” – ጌታነህ ከበደ

ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ከሶከር ኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው መመለሱን በትናንትናው ዕለት አውቋል። ቡድኑም የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን አቢጃን ላይ አድርጎ ዛሬ ምሽት 2:45 አዲስ አበባ ደርሷል። እኛም ከቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ጋር ከተደረገው ቆይታ የተቀነጨበውን ሀሳብ እንዲህ ቀርበናል።

“እኔ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የአሁኑ ቡድን በጣም የተሻለው ነው። ምክንያቱም ቡድኑ ኳስ የሚጫወት ቡድን ነው። በተጨማሪም በየቦታው ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ። በሜዳችንም ተጋጣሚዎቻችንን በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፋችን ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንድናልፍ ጠቅሞናል።

“የእኛ ጨዋታ 81ኛው ደቂቃ ላይ ከተቋረጠ በኋላ የኒጀርን ውጤት ሰምተን ነበር። እኛ እንደውም የቀረውን ደቂቃ ረስተን ወደ መጨፈሩ ነበር ያመራነው። ግን ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ የቀረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመስመር ዳኛው መሪነት እንዲከናወን ሆኗል።”

ከአምበሉ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በነገው ዕለት ይዘን የምንመለስ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ