የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስድስት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ ሁሉንም ደቂቃዎች የተጫወቱት ተጫዋቾች እንማን ናቸው?
በካሜሩን አስናጋጅነት ለሚደረገው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ከኮትዲቯር፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር በምድብ ተደልድሎ ጨዋታዎችን ሲያከናውን የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትላንትናው ዕለት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚወስደውን ትኬት መቁረጡ አረጋግጧል። ብሔራዊ ቡድኑም ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለመመለስ ለ16 ወራት የቆየውን የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ማከናወን ግድ ብሎታል። በዚህም ህዳር 6 2012 አንታናናሪቮ ላይ የተጀመረው የቡድኑ ተልዕኮ መጋቢት 21 2013 አቢጃን ላይ ተገባዷል። ታዲያ ቡድኑ በዚህ ረጅም የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ሁለት አሠልጣኞችን (ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና ውበቱ አባተ) እና ሠላሳ ሜዳ ገብተው የተጫወቱ ተጫዋቾችን ተጠቅሟል። ሜዳ ገብተው ከተጫወቱት ሠላሳ ተጫዋቾች መካከልም እያንዳንዱ ደቂቃ (540) ላይ ተሳትፎን ያደረጉትን ብቸኞቹን ተጫዋቾች ለይተን ይዘን ቀርበናል።
ቡድኑ ያደረጋቸው ስድስቱም የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው የመጀመሪያው ተጫዋች የመሐል ተከላካዩ አስቻለው ታመነ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊሱ የኋላ ደጀን ብሔራዊ ቡድኑ ከአንታናናሪቮ ጀምሮ ያደረገው እያንዳንዱ ደቂቃ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል። በቅድሚያ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሁለት ጨዋታዎች ላይም ከአንተነህ ተስፋዬ እና ደስታ ደሙ ጋር ተጣምሮ ተጫውቷል። በአሃዝም ተጫዋቹ በአብርሃም ስር በተጫወታቸው 180 ደቂቃዎች ውስጥ 156ቱን ከአንተነህ ተስፋዬ ጋር፤ 24ቱን ደግሞ ከደስታ ደሙ ጋር አሳልፏል። የብሔራዊ ቡድኑን የአሠልጣኝነት መንበር የተረከቡት ውበቱ አባተ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ህዳር 4 ቀን 2013 ኒያሜ ላይ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ 360 ደቂቃዎችን ከያሬድ ባየ ጋር ተጫውቷል። በአጠቃላይም ተጫዋቹ ቡድኑ በማጣሪያ ባደረጋቸው 540 ደቂቃዎች ላይ ተሳትፎን ያደረገ በሚል ስሙን አፅፏል።
እንደ አስቻለው ታመነ ሁሉ በስድስቱም ጨዋታ ላይ ተሳትፎ የነበረው ሌላኛው ታሪካዊ ተጫዋች ረመዳን የሱፍ ነው። የወልቂጤ ከተማው የግራ መስመር ተጫዋች ረመዳን ያለ ከልካይ የብሔራዊ ቡድኑን የግራ መስመር ተከላካይነት ቦታ ተቆጣጥሮ ይገኛል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በስድስቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ አጠቃላይ አራት የመስመር ተከላካዮችን (አህመድ ረሺድ፣ አሥራት ቱንጆ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ረመዳን የሱፍ) ተጠቅሟል። በዚህም ከረመዳን ውጪ የተጠቀሱት ሦስቱ ተጨዋቾች በተለያዩ አጋጣሚዎች የቡድኑን የቀኝ መስመር ተከላካይነት ቦታ ሲይዙ የነበረ ሲሆን ረመዳን ግን በሁሉም ጨዋታዎች የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ የተሰለፈ ነበር። ከኳስ ጋር ባለው ምቾት፣ ለማጥቃት ባለው ፍላጎት እና የመከላከል አቅሙ በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ውበቱ አባተ ተቀዳሚ ተመራጭ የነበረው ተጫዋቹም እንደ አስቻለው በሁሉም የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሌላኛው ብቸኛ ተጫዋች በሚል ተመዝግቧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ