“በመጨረሻው ደቂቃ የእነሱን ውጤት ነበር ስንከታተል የነበረው” – ውበቱ አባተ

በአሁኑ ሰዓት ከአቢጃን የአምስት ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ በረራ አድረገው አዲስ አበባ የደረሱትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚመሩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በትላንቱ ጨዋታ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ቡድኑ ውስጥ የተፈጠረውን ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አቢጃን ላይ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ገብተዋል። ልዑኩን የያዘው ቦይንግ 787 አውሮፕላን ቦሌ የአየር ማረፊያ ሲደር በስፍራው የነበረችው ሶከር ኢትዮጵያ የቡድኑን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተን አግኝታ አጫጭር ጥያቄዎችን አቅርባለች። ለአሁንም የትላንቱ ጨዋታ ከተቋረጠ እና የኒጀር ጨዋታ ከተገባደደ በኋላ ቡድኑ ላይ የነበረውን ስሜት በተመለከተ ጥያቄ አቅርባ የተሰጠውን ምላሽ ይዛ ቀርበናል።

“በጣም ከባድ ነው። የእኛ ጨዋታ እንደተቋረጠ የማዳጋስካር እና የኒጀር ጨዋታ ባዶ ለባዶ እንደሆነ ሰምተናል። ይህም ቢሆን ግን ትኩረታችን ሜዳ ላይ እየተፈጠሩ ባሉት ነገሮች ነበር። በመጨረሻው ደቂቃ ግን የእነሱን ውጤት ነበር ስንከታተል የነበረው። በመጨረሻም ውጤቱን ሲሰሙ ብዙ ተጫዋቾችም ያለቅሱ ነበር። በጣም በውጥረት ላይም እንደነበሩ ያወኩት በዛ ሰዓት ነው። ሰበብ ለማድረግ ሳይሆን ጨዋታው በከፍተኛ ወበቅ የተደረገ ነው። ተጫዋቾቼም እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አልቻሉም። ዳኛው ላይም የተፈጠረው ይህ ነው። በአጠቃላይ ግን ደስታው ልዩ ነበር።”

የአሰልጣኝ ውበቱን ሙሉ ቃለ ምልልስ በነገው ዕለት ይዘን እንቀርባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ