ዩናይትድ ቤቬሬጅስ ለአዳማ ከተማ የትጥቅ ድጋፍ አደረገ

በዛሬው ዕለት ወደ ድሬዳዋ የሚያመሩት አዳማ ከተማዎች ትላንት ምሽት የሽኝት ፕሮግራም ሲደረግላቸው ዩናይትድ ቤቬሬጅስም የትጥቅ ድጋፍ አድርጎላቸዋል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ደካማ ብቃት በማሳየት በወራጅ ቀጠናው ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በድሬዳዋው እና ሀዋሳው ቀጣይ ውድድር ተጠናክሮ ለመቅረብ የተጫዋቾች ዝውውር ሲያከናውኑ መቆየታቸው ይታወሳል። ቡድኑም በተነቃቃ ስሜት ወደ ድሬዳዋ እንዲጓዝ በቅርቡ በይፋዊ ሥነ-ስርዓት የክለቡ ስፖንሰር እንደሚሆን የተገለፀው አምበሳ ቢራ የሽኝት እና የእራት ግብዣ መርሐ-ግብር በትላንትናው ዕለት አከናውኗል።

በኢሊሌ ሆቴል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የአምበሳ ቢራ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ኡርጌሳ፣ የተቋሙ የሽያጭ ሀላፊ አቶ ኤፍሬም ትዛዙ፣ የአዳማ ከተማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። የእራት መርሐ-ግብሩ ከተከናወነ በኋላም የአምበሳ ቢራ አምራች የሆነው ዩናይትድ ቤቬሬጅስ ለክለቡ በጃኮ ካምፓኒ የተመረተ ሁለት አዲስ የመጫወቻ መለያዎች፣ የልምምድ መለያዎች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሚለብሱትን መለያ በስጦታ መልክ ሰጥቷል። ስጦታውንም የቡድኑ አሰልጣኝ ዘርዓይ፣አምበሉ ኤሊያስ እና ግብ ጠባቂው ካማራ ሴኩምባ ተቀብለዋል። በምስሉ ላይ የክለቡ ስፖንሰር እንደሚሆን የተገለፀው አንበሳ ቢራ አርማ ባያርፍም ዛሬ አልያም ነገ የተቋሙ ስም በመለያው ላይ አርፎ ቡድኑ የድሬዳዋውን ውድድር እንደሚጀምር ተነግሯል።

በተጨማሪም በእራት ግብዣው ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ተጫዋቾች ክለቡን ከመውረድ ካዳኑ ከፍተኛ ሽልማት እንደሚዘጋጅላቸው መግለፃቸውን ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ