የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የሰበታ ኮንትራት ጉዳይ?

👉”…ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስፈራረም አንድ ስህተት ፈፅሜያለሁ…” ውበቱ አባተ

👉”አሠልጣኙ ሳይጨነቅ ነጻ ሆኖ የሚሰራበት ዕድል ለማመቻቸት እንሞክራለን” ባህሩ ጥላሁን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ዛሬ ከቀጥር በኋላ የብሔራዊ ቡድኑን የመጨረሻ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ግለሰቦቹ ሀሳባቸውን ካስተላለፉ በኋላም መግለጫውን ሲከታተሉ የነበሩ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ሲያነሱ ነበር። ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተን እና እስካሁን ያለተቋጨውን የሰበታ ከተማ ውል የተመለከተው አንዱ ነው። ይህንን ጥያቄ በተመለከተም አቶ ባህሩ ጥላሁን በቀዳሚነት ተከታዩን አጭር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“አንድ ክለብ ውስጥ የሚገኝ አሠልጣኝ ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ የሚፈለግ ከሆነ ክለቡ አሠልጣኙን እንዲለቅ የሚያደርግ የተፃፈ ነገር አለ። ፌዴሬሽኑም ይህንን በመከተል ነው አሠልጣኙ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንዲመጣ ያደረገው። እርግጥ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህንም ጥያቄዎች አሁን ላይ የምንመለከታቸው ይሆናል። በአጠቃላይ አሠልጣኙ ሳይጨነቅ ነጻ ሆኖ የሚሰራበት ዕድል ለማመቻቸት እንሞክራለን።” ብለዋል። የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አጠር ያለ ማብራሪያቸውን ከሰጡ በኋላ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ዘለግ ላለ ደቂቃ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

“እኔ ከዚህ ቀደም ኮንትራቶችን ስፈርም በጣም ተጠንቅቄ ነው። በቃል ከተስማማሁም በኋላ ብዙ ጊዜ የሚፈጅብኝ ዝርዝር የኮንትራቱ ጉዳይ ነው። ይህንን ደግሞ በተለያዩ ክለቦች ስፈርም አድርጌዋለሁ። አሁን ግን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስፈራረም አንድ ስህተት ፈፅሜያለሁ። እሱም የነበረኝን የሰበታ ኮንትራት በግልፅ ሳልቋጭ ይህኛውን ውል መፈረም አልነበረብኝም። እርግጥ ይህንን ስህተት የፈፀምኩት ከጊዜ ጋር ባለ ሩጫ ነው። የሰበታው ውል እስኪቋጭ ከጠበቅን የኒጀሩ ጨዋታ ሊደርስ ሆነ። በወቅቱም የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ‘የሰበታን ነገር ለእኛ ተወው። አንተ ብቻ ሥራህ ላይ አተኩር’ ስላሉኝ ነው።

“እንደሚታወቀው ሰበታ ለሁለት ዓመት ነበር የፈረምኩት። አንድ ዓመት ደግሞ ሰርቻለሁ። ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ጋር ውል ያሰርኩት ብሔራዊ ግዳጅ ስለሆነ ነው። እንድታቁልኝ የምፈልገው ነገር ውስጤ ጥሩ አልነበረም። ጉዳዩ በቶሎ እንዲፈታም የተለያዩ ጥረቶችን አድርጌያለሁ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንንም በደብዳቤ ጠይቄያለሁ። በተጨማሪም ጉዳዩን ሊፈቱልኝ ይችላሉ ያልኳቸው ሰዎች ጋር ሄጇለሁ። እንደውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ልቀቁኝ እና ሰርቼ ልክፈላቸው ብዬ ነበር። ግን በተተራመሰ ሀገር ሌላ ትርምስ አልፈጥርም ብዬ ተውኩት። በተጨማሪም ስራው ይሰራ ብዬ ነው። አንዳንድ ሚዲያዎች ግን እንዳጭበረበርኩ እያደረጉ ሲያወሩ ነበር። ይህ ልክ አደለም። ሰበታዎች እንኳን እንደነሱ አላስጨነቁኝም። አሁን ስራው አልቋል። ከዚህም በኋላ በሰከነ መንገድ ንግግሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ