“ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፍነው ቀን እና ለሊት ሠርተን ነው” – ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን ተከትሎ ከመጨረሻ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ ሰጥተዋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ማረጋገጡ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የቡድኑን የምድብ የማጣሪያ ሂደት በተለይም የመጨረሻዎቹን የማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጨዋታን በተመለከተ ወሎ ሠፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከአንድ ሰዓት በላይ በቆየው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመጀመሪያ ሀሳባቸውን በሰፍራው ለሚገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ያጋሩት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባታ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ወደፊት ቡድናቸው በማጣሪያ ጨዋታዎቹ የነበረውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በቴክኒክ እና ማስረጃ በተደገፈ መዘርዝር ለማብራራት ሀሳብ እንዳላቸው ገልፀዋል። አሠልጣኙ ቀጥለውም ከመጨረሻዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎችን የተመለከተ ገለፃቸውን ማድረግ ይዘዋል።

“እንደምታስታውሱት ሊጉ ክፍተት በሚሰጠን ጊዜ ተጫዋቾችን እየሰበሰብን ልምምዶችን ስንሰራ ነበር። ሊጉ የባህር ዳር ቆይታውን ካገባደደ በኋላም ተጨማሪ ልምምዶችን ሰርተን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር አድርገናል። በጨዋታውም ራሳችንን በደንብ አይተናል። ቡድኑም የተወሰነ ችግር የነበረበት ግብ የማስቆጠሩ ሂደት ላይ ነበር። በዚህም ላይ ስራዎችን ሰርተናል። ከዛም ከማዳጋስካር ጋር የምድቡን አምስተኛ ጨዋታ ከውነናል። ጨዋታውንም በሙሉ ብልጫ አሸንፈን ወጥተናል። በመቀጠል የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ለማድረግ ወደ አይቮሪኮስት ነው ያመራነው። ከጨዋታውም ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት አስበን ነበር። ግን በጥቃቅን ስህተቶች በተቆጠሩብን ጎሎች ተሸንፈናል። ይህም ቢሆን ግን ኒጀር እና ማዳጋስካር አቻ በመለያየታቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫው አልፈናል።” አሠልጣኙ ጨምረውም ቡድኑ በሁለት ጨዋታ አምስት ጎል አስቆጥሮ ሦስት ብቻ ማስተናገዱን አስታውሰው ማጥቃቱ ላይ ጥሩ እንደነበሩ አብራርተዋል። ከውበቱ አባተ ንግግር በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተቋማቸው (ፌዴሬሽኑ) ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንዲያልፍ ያከናወናቸውን ሥራዎች ማብራራት ጀምረዋል።

“ፌዴሬሽናችን ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በአትኩሮት ሲከውን ነበር። ይህኛውም የአሠልጣኝ ቡድን ሲዋቀር ዋናውን አሠልጣኝ እንዲያግዙ እና እንዲረዱ የተለያዩ ባለሙያዎችን ቀጥረናል። በዚህም የስነ-ምግብ ፣ የአካል ብቃት፣ የስነ-ልቦና እና የቪዲዮ አናሊስት ባለሙያዎችን የአሠልጣኝ ስብስቡን እንዲቀላቀሉ አድርገናል። እርግጥ ይህ በቂ ነው ብለን አናስብም። ግን እንደ አቅማችን ብሔራዊ ቡድኑን የሚጠቅሙ ባለሙያዎችን ቀጥረናል።

“ከማዳጋስካሩ እና አይቮሪኮስቱ ጨዋታ በፊት ደግሞ አሠልጣኙ ተጫዋቾችን ሰብስቦ በሦስት ዙር ልምምድ ማሰራት ሲፈልግ የተለያዩ እገዛዎችን ስናደርግ ነበር። በተጨማሪም ቡድኑ አቋሙንን እንዲገመግም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንዲጫወት አድርገናል። በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጠየቁትን አብዛኛውን ነገሮች ለሟሟላት ሞክሯል።”

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አቶ ባህሩ ጥላሁን ከአስር ደቂቃ ያልዘለለ አስተያየታቸውን ካሰሙ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫውን እየተከታተሉ የነበሩ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል። ግለሰቦቹም ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሾቸን መስጠት ቀጥለዋል።

ስለ ቡድኑ የተከላካይ መስመር ድክመት?

“እውነት ለመናገር እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ብሔራዊ ቡድኖች ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ አልነበረንም። ይህም ቢሆን ግን ባለን ጊዜ ሂደቱን የጠበቀ ቡድን ለመገንባት ስንሞክር ነበር። በዚህም መሻሻሎችን አይተናል። ከማዳጋስካሩ እና አይቮሪኮስቱ ጨዋታ በፊት ትኩረታችን ሙሉ ለሙሉ ማጥቃቱ ላይ ነበር። ምክንያቱም የማዳጋስካሩን ጨዋታ ማሸነፍ ነበረብን። ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከሁለት በላይ ጎሎችን ማስቆጠር ነበረብን። ያለበለዚያ ግን ቀጣዩ የአይቮሪኮስት ጨዋታ ዋጋ አይኖረውም ነበር። ከዚህ መነሻነት ማጥቃቱ ላይ ትኩረት ሰጥተን ነበር። እንደውም አንዳንድ ተጫዋቾች ‘መከላከሉ ላይስ?’ የሚል ሀሳቦችን ሲያነሱልኝ ነበር። አሁን ያልኩትንም ነገር ለተጫዋቾቹ አስረድቻቸዋለሁ። እኛ ግን የወሰድነው ውሳኔ ጠቅሞናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኋላ አካባቢ ክፍተቶች ነበሩ። ወደፊት ግን የፈለገ ግብ ብናስቆጥር የሚቆጠርብን ከሆነ ዋጋ የለውም። ስለዚህ ይህንን የመከላከል ክፍተት እናስተካክላለን።” ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቡድኑን ለማገዝ ምን እየሰራ ነው?

“ዋናው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ችግር ፋይናንስ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ እንደ ተቋም እየቀየስናቸው ያሉ ነገሮች አሉ። በተለይም በቀጣይ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥሩ ነገር እንዲገጥመው ስራዎችን እንሰራለን። ከምንም በላይ ሊጉ ተጠናቆ በሚኖረው ክረምት ቡድኑ ሳይበተን ተሰባስቦ ልምምዶችን እንዲያደርግ እንጥራለን።

“ከገንዘብ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ እቅዶች አሉት። ለምሳሌ በክልል ለመዞር አስበናል። በዚህም የተለያዩ የክልል ፕሬዝዳንቶችን ለማናገር እንሞክራለን። በተጨማሪም ባለሀብቶችንም እናናግራለን። ይህ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የስፖንሰሮችን በር ለማንኳኳት እንጥራለን። ስለዚህ ከፊፋ እና ካፍ በሚገኝ ገንዘብ ብቻ ብሔራዊ ቡድናችንን አንገነባም። በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑን በፋይናንስ አጠናክረን ብሔራዊ ቡድኑን ለመደገፍ እንሞክራለን።” ባህሩ ጥላሁን

ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንዲያልፍ ስለተሰሩት አጠቃላይ ሥራዎች?

“ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስናልፍ ቀን እና ለሊት ሰርተን ነው። ከባለሙያ ምርጫ ጀምሮ እያንዳንዱን ነገር በአትኩሮት ነው የሰራነው። የተጫዋች ምርጫ ላይም እንደዛው። የሚገርማችሁ ገና በፊት መጀመሪያ ከተጫዋቾች ጋር ስናወራ አላማችን ካሜሩን እንደሆነ ነግሬያቸዋለሁ። እንደውም ያልኳቸው እናንተ ካሜሩን መሄድ ከፈለጋችሁ እሰየው ካልሆነ ግን እኔ በራሴ ትኬቴን ቆርጬ እሄዳለሁ ነው። ስለዚህ ከመጀመሪያ ጀምሮ አቅደን ነው የተነሳነው። ቢያንስ መጀመሪያችንን እና መጨረሻችንን አውቀን ነበር ሠሥንሰራ የነበረው።” ውበቱ አባተ

ስለ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ እንቅስቃሴ?

“ተክለማርያም ሦስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ግን መዘንጋት የሌለብን ሦስት ጨዋታ ላይ ግብ አለማስተናገዱን ነው። ስለዚህ ጎል ሲቆጠርበት ብቻ ችግሮችን ማንሳት የለበትም። ተጫዋቹ ወደፊት ስህተቶቹን እንዲቀንስ እንረዳዋለን። ቦታውም ርስት አደለም። ሌሎቹንም ግብ ጠባቂዎች በተለያዩ ጨዋታዎች እናያቸዋለን። እንዳልኩት ግን እሱንም እንዲሻሻል እንረዳዋለን። ውበቱ አባተ

ስለ ቀጣይ የዝግጅት ጊዜ?

“ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ድሬዳዋ ቀረብ በማለት ስራዎችን እንሰራለን። የብሔራዊ ቡድኑን ተጫዋቾች እና ሊመረጡ የሚችሉ ተጫዋቾችን አንድ ለአንድ ከማናገር ጀምሮ ሥራዎችን እንሰራለን።” ውበቱ አባተ


© ሶከር ኢትዮጵያ