የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነው ጌታነህ ከበደ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን ተከትሎ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበንለት የሰጠንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ዋልያዎቹ ከትናንት በስትያ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ከአይቮሪኮስት ጋር ካከናወኑ በኋላ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል። ብሔራዊ ቡድኑ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላም የተለያዩ አካላት የአቀባበል ሥነ-ስርዓት እያደረጉለት ይገኛሉ። ልዑካኑም ትናንት ምሽት 2:45 አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በነበረ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ለቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርባለች። ተጫዋቹም ለጥያቄዎቹ የሰጠውን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ወደ አፍሪካ ዋንጫው በማለፋችሁ ምን ተሰማህ?
“በጣም ደስ ብሎናል። ከዚህ ቀደም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፍነው በጣም በረጅም ጊዜ ነበር። አሁን ደግሞ በቅርብ ጊዜ ልዩነት ወደ አህጉሪቱ ውድድር አልፈናል። በዚህም ደግሞ በጣም ደስ ብሎኛል።”
2013 ላይ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሲያልፍ የነበረውን እና አሁን ያለው ስሜት አነፃፅርልን?
“ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስናልፍ የነበረው የደስታ ስሜት ለየት ይል ነበር። ምክንያቱም ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ውድድሩ ስለተመለስን። የአሁኑም ግን በጣም ደስ ይላል። በተለይ ከሜዳችን ውጪ የመጨረሻ ጨዋታችንን ማድረጋችን ትንሽ አስጨንቆን ነበር። እንደምታስታውሰው ያኔ የመጨረሻ ጨዋታችንን ያደረግነው በሜዳችን እና በደጋፊያችን ፊት ነበር። አሁን ግን ይህ አልነበረም። በሌላ በኩል ደግሞ የአሁኑ ላይ የእኛ ውጤት ብቻ አልነበረም ወሳኙ። የማዳጋስካሩም ጨዋታ ለእኛ ጥሩ ነገር ይዞ ስለሚመጣ እንደ ያኔው ሙሉ ትኩረታችን በጨዋታው ላይ ብቻ አልነበረም። ይህንን ብልም ግን ደስታው አስፈንድቆናል።”
ወደ አፍሪካ ዋንጫው ብሔራዊ ቡድኑን የመለሰው የአሁኑ ስብስብ ምን ይመስላል?
“እኔ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የአሁኑ ቡድን በጣም የተሻለው ነው። ምክንያቱም ቡድኑ ኳስ የሚጫወት ቡድን ነው። በተጨማሪም በየቦታው ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ። በሜዳችንም ተጋጣሚዎቻችንን በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፋች ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንድናልፍ ጠቅሞናል።”
የአይቮሪኮስቱ ጨዋታ ተቋርጦ የኒጀርን እና የማዳጋስካርን ውጤት ስትሰማ ምን ተሰማህ?
“የእኛ ጨዋታ 81ኛው ደቂቃ ላይ ከተቋረጠ በኋላ የኒጀርን ውጤት ሰምተን ነበር። እኛ እንደውም የቀረውን ደቂቃ ረስተን ወደ መጨፈሩ ነበር ያመራነው። ግን ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ የቀረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመስመር ዳኛው መሪነት እንዲከናወን ሆኗል።”
ብሔራዊ ቡድኑ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ መሸነፉ ደስታችሁን አደብዝዞታል?
“በጭራሽ። ስሜታችን አልቀዘቀዘም። አይቮሪኮስትን እኮ እኛ እዚህ አሸንፈነው ነበር። እነሱ ደግሞ በሜዳቸው አሸነፉን። ይህ ደግሞ በእግር ኳስ ያለ ነው። መርሳት የሌለብን ነገር ደግሞ ቡድኑ ትልቅ መሆኑን ነው። ከየትኛውም የዓለማችን ቡድን ጋር ቢጫወት ሊያሸንፍ ይችላል። በስብስቡም ያሉት ተጫዋቾች በታላላቅ ክለቦች የሚጫወቱ ናቸው። ከዚህ መነሻነት የመጨረሻው ሽንፈት ብዙም አላስከፋንም።”
ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉ ለእግር ኳሱ ምን ፋይዳ ያመጣል?
“ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንደ መስራችነቷ ሁሌ በውድድሩ መገኘት አለባት። ይህንን ደግሞ ለማድረግ አቅሙ አለን። በተለይ አሁን እየመጡ ያሉት ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ጥሩ ናቸው። ዘንድሮ ደግሞ ሊጉ በዲኤስ ቲቪ መተላለፉ የጠቀመን ይመስለኛል። ስለዚህ የዘንድሮውን ማሳያ ይዘን በቀጣይ ረጅም ዓመታት ከውድድሩ ላለመራቅ እና ቋሚ ተሳታፊ ለመሆን መስራት አለብን።”
የኢትዮጵያ ህዝብ ከአፍሪካ ዋንጫው ምን ይጠብቅ?
“እንደ በፊቱ በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ብቻ አንሄድም። ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደምንሄድ አስባለሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ቡድኑም ይህንን ነው የሚያስበው። ስለዚህ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሻለ ቡድን ለማሳየት እንሞክራለን። የኢትዮጵያም ህዝብ የተሻለ ነገር እንዲጠብቅ መርዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።”
ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው የተሻለ ርቀት እንዲጓዝ ምን ማስተካከል አለበት?
“ቡድናችን ውስጥ ያለው ድክመት የተወሰ ነው። ከምንም በላይ ግን የቅጣት ምቶች፣ የመዓዘን ምቶች እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ድክመቶች አሉብን። ይህንን ማስተካከል አለብን። እርግጥ ከሜዳችን ውጪ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይም ችግሮች አሉብን። ግን የአፍሪካ ዋንጫው ላይ የሜዳ ጥቅም የሚባል ነገር የለም። ከአዘጋጇ ሀገር ውጪ ሁሉም ከተለያየ ቦተ የሚመጡ ናቸው። ስለዚህ ነገርየው ለሁሉም ቡድን ይሰራል። በአጠቃላይ ግን የጠቀስኩትን እና ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችን ካስተካከልን ጥሩ ቡድን በውድድሩ ላይ ይዘን መቅረብ እንችላለን።”
© ሶከር ኢትዮጵያ