የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሰሞነኛ የትኩረት ነጥቦች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2013 ሁለተኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ በተለያዩ ከተሞች እየተደረጉ ይገኛሉ ። በዚህ ውድድር ላይ ሰሞኑን የተመለከትናቸውን ዋና ዋና ነጥቦችም በዚህ መልኩ አሰናድተናል። 

👉 ለውድድሩ በቂ ትኩረት ያልሰጡት ቡድኖች

በሀገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ሁለት ቡድኖች ወደ ቦታው ማምራት በሚጠብቅባቸው ጊዜ ባለማምራታቸው ምክንያት ፎርፌ ተሰጥቶባቸዋል። በምድብ ለ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ሳምንት አቃቂ ቃሊቲ ከ ጅማ አባ ቡና እንዲሁም ሶዶ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ሊደረጉ የነበሩት ጨዋታዎች ላይ አቃቂ እና ሶዶ በበቦታው ባለመገኘታቸው ምክንያት የፎርፌ ተሸናፊ ሆነዋል።

👉 ቆራጥነት የታየበት ውሳኔ

በከፍተኛ ሊግ ውድድር ያለፉት ዓመታት እንደ ድክመት ከሚነሱት ጉዳዮች አንዱ ቡድኖች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በወቅቱ የመክፈል ችግር መሆኑ ይታወቃል። ቡድኖች በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በወቅቱ ማጠናቀቅ ካልቻሉ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረው ክፍያቸውን ሲያጠናቅቁ ጨዋታዎቹ ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ይህም ቡድኖች ክፍያ አለመክፈል የሚያመጣባቸው ቅጣት ባለመኖሩ ቸልተኛ ሲሆኑ እና ውድድሮች ያለአግባብ ሲፋለሱ ቆይተዋል።

በዚህ የውድድር ዓመት አጋማሽ ይህን በተመለከተ በጁፒተር ሆቴል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የከፍተኛ ሊግ ዋና ሰብሳቢ ዓሊሚራ መሐመድ፣ ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ባሉበት ክፍያ ያላጠናቀቀ ቡድን በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል። የዚህም በትር በከንባታ ሺንሺቾ የወደቀ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ስልጤ ወራቤን ሊገጥም የነበረው ሺንሺቶ ክፍያ ባለመፈፀሙ ወራቤ ቡድን ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ተወስኗል።

👉 ኮቪድ 19 የፈተነው ሊግ

በነቀምቴ እየተደረገ የሚገኘው የምድብ ሐ እንዲሁም በወልዲያ እየተከናወነ የሚገኘው ምድብ ለ በኮሺድ ምርመራ ላይ ተግዳሮቶች እየታየባቸው ይገኛል። ከተሞቹ ኃላፊነት ወስደው ውድድሩን ወደ ቦታቸው ሲወስዱ ቃል ከገቡባቸው ጉዳዮች መካከል የኮቪድ ውጤት በጊዜው ማድረስ ቢሆንም ይህ ክንውን እክል ገጥሞታል። በዚህ ችግር ምክንያት በምድብ ለ የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአንድ ቀን ሲሸጋሸጉ ቡታጅራ ከተማ ከቂርቆስ ሊያደርጉት የነበረ የምድብ ሐ ጨዋታም ሳይካሄድ ቀርቶ በተስተካካይ መርሐ ግብ ዛሬ ተደርጓል።

የከፍተኛ ሊጉ ከውጤት በጊዜው አለመድረስ ባሻገር ቡድኖች በርካታ ተጫዋቾቻቸው በኮቪድ በመጠቃታቸው ምክንያት ሳይካሄዱ የቀሩባቸው አጋጣሚዎችም ተከስተዋል። አርባምንጭ ከሺንሺቾ ምድብ ሐ እንዲሁም ሻሸመኔ ከነቀምቴ በምድብ ለ ሊደረጉ የነቀሩ ጨዋታዎች አርባምንጭ እና ሻሸመኔ በርካታ ተጫዋቾቻቸው በኮሮና በመያዛቸው ሳይካሄዱ ቀርተዋል።

👉 የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች በመከላከያ

ረዘም ላሉ ዓመታት በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ በመቅረብ የሚታወቀው መከላከያ ይህ ባህሉን በዚህ ዓመት በመተው የውጪ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሎ ማጫወት ጀምሯል።

በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ጦሩ አራት የውጲ ዜጎች ያስፈረመ ሲሆን ሜዳ ገብተው ተጫውተውም ተመልክተናል። ኤርነስት ባራፎ ፣ ሰሎሞን ዴቪድ፣ አልሀሰን ኑሁ እና መሐመድ አብዱላሂ የመከላከያ አዳዲስ ፈራሚ የውጪ ዜጎች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ