የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዛሬ ውሎ…

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ የተደረጉትን የየምድብ ጨዋታዎች እንዲህ ተመልክተናቸዋል፡፡

በምድብ ሀ የአስራ ሦስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲን 3፡00 ሲል ያገናኘው ጨዋታ ቀዳሚው ነበር፡፡ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ማራኪ የቅብብል አጨዋወቶችን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኤሌክትሪኮች ብልጫ መውሰድ ቢችሉም በመጀመሪያው አጋማሽ ይታይባቸው የነበረው የአጨራረስ ድክመት ቡድኑ ያገኛቸውን ቀላል የማይባሉ ዕድሎች ወደ ጎልነት እንዳይለወጥ አድርገውታል። የጨዋታ መንገዳቸውን በይበልጥ ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል በፈጣኑ ተጫዋች ኤርሚያስ ኃይሉ በኩል አድርገው መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ኳስን ወደ ጎል ነድቶ ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ወጥነት ይጎለው ስለነበር የተገኙትን ኳሶች የለገጣፎ ተከላካዮች በረጅሙ ወደ አጥቂ ክፍላቸው በመጣል በተቃራኒው የግብ ዕድልን በማግኘቱ ረገድ ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ታይተዋል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ ተከላካይ ወልደአማኑኤል ጌቱ በረጅሙ የመጣችን ኳስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ በሳዲቅ ተማም ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት ቀለመወርቅ መትቶ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ መልሶበት ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን አማካዩ ፍፁም ቅጣት ምቱን ቢስትም 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች የተሻሉ መሆናቸውን ባደረጉት ፈጣን እንቅስቃሴ ማስተዋል የቻልን ቢሆንም ይፈጥሯቸው የነበሩ የመከላከል ስህተቶች በዚህኛውም አጋማሽ ጎል እንዲቆጠርባቸው አድርጓል፡፡ከዕረፍት ከተመለሱ አራት ያህል ደቂቃ እንደተቆጠረ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ከግብ ክልል ባለማራቃቸው ሣዲቅ ተማም እግር ስር ገብታ አጥቂው የቀድሞው ክለቡ ላይ ጎል ሲያስቆጥር የቡድኑን የግብ መጠን ደግሞ ወደ ሁለት አሳድጓል፡፡ ሁለት ለምንም ለመመራት የተገደዱት ኤሌክትሪኮች አከታትለው ተጫዋቾችን ከቀየሩ በኋላ ጨዋታውን በሚገባ በመቆጣጠር ለማንሰራራት እጅጉን ኃይላቸውን በሙሉ በመጠቀም ተጫውተዋል፡፡ 57ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ በግሩም ቅብብል በግራ መስመር በኩል ዓለምነህ ግርማ ወደ ጎል ሲያሻማ ሀብታሙ ጥላሁን አግኝቶ በቀጥታ መትቶ አብርሃም ኩማ በሚገርም ብቃት ቢመልስም ኳሷን ባለመቆጣጠሩ ኤርሚያስ ኃይሉ በፍጥነት ደርሶ ወደ ጎልነት በመቀየር ኤሌክትሪክን ወደ ጨዋታ መልሷል፡፡ ቶሎ ቶሎ ብልጫን ወስደው ወደ ግብ ክልል ሲደርሱ የታዩት የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ልጆች በወጣቱ ፀጋ ደርቤ ጎል አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ ከተባለ ስምንት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ማለትም 90ኛው የጨዋታው ማብቂያ ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ በግራ የለገጣፎ የሜዳ ክፍል ወደ ጎል ሲያሻግር አደም አባስ በሚገርም ቄንጠኛ ጎል ኤሌክትሪክን 2-2 በማድረግ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ሁለተኛው የምድቡ ጨዋታ ከሰዓት ቀጥሎ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን ከፌደራል ፖሊስ ጨዋታቸውን አድርገዋል፡፡ ኳስ ከመንሸራሸር ውጪ የተሳኩ የሙከራ ዕድሎችን መመልከት ባልቻልንበት ጨዋታ በአንፃራዊነት ፌደራል ፖሊሶች ወጥነት አይታይባቸውም እንጂ ወጣ ገባም እያሉ የጎል ሙከራን ለመፍጠር ዳድተዋል፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ 26ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ታሪኩ ከማዕዘን ምት ሲያሻማ አቤል አየለ በግንባር ገጭቶ በለጠ ተስፋዬ ያዳነበት አጋጣሚ ቡድኑ በዚህኛው አጋማሽ ቡድኑ ያደረገው ጥሩ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን እንደ ቀዳሚው አርባ አምስት ሁሉ ያላየንበት ቢሆንም በሚገኙ ውስን ዕድሎች አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ፌደራል ፖሊሶች ሻል ያሉ ነበሩ፡፡ 59ኛው ደቂቃ ላይ የደብረብርሃኑ ተጫዋች ሥዩም ደስታ በፌደራል ተጫዋች ላይ በክርኑ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ በሁለተኛ ረዳት ዳኛው ጥቆማ ሊወገድ ችሏል፡፡ ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በተሻለ መልኩ አቀራረባቸውን ያሳመሩት ፖሊሶች 88ኛው ደቂቃ ላይ በተመስገን ታሪኩ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በተገኘች ኳስ ግብ አግኝተው ጨዋታው 1-0 ሊጠናቀቅ ችሏል።

በምድብ ሁለት ካፋ ቡናን የገጠመው ሀምበሪቾ 2-0 በማሸነፍ አአ ከተማን መከተሉን ቀጥሏል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር 71ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ጌታቸው ሁለተኛውን አክሏል።

ሀላባ ከተማ አዩብ በቀታ እና ኪዳኔ አሰፋ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-1 ሲያሸንፍ ጋሞ ጨንቻ ሶዶ ከተማን 4-1 ረቷል። አሸናፊ ተገኝ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ዘላለም በየነ እና በድሉ ሰለሞን ቀሪዎቹን አስቆጥረዋል።

በምድብ ሦስት መድን በቡታጅራ ተሸንፎ ተከታታይ ሽንፈቱን ቀምሷል። 2-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ሙሴ እንዳለ እና በረከት ግዛው ቡታጅራን ባለድል ሲያደርጉ ቶሎሳ ንጉሤ ለመድን አስቆጥሯል። የካ የዮሐንስ ደረጀ ጎል ሺንሺቾን 1-0 ሲያሸንፍ ደቡብ ፖሊስ ከባቱ በኮቪድ ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ