የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ልምምድ ጀምሯል

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በ2022 ለሚከናወነው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያዎችን ወደፊት በሚገለፅ ቀን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረፋድ ልምምድ ጀምሯል።

በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው አማካኝነት ከቀናት በፊት ጥሪ የቀረበላቸው ተጫዋቾች ትናንት በካፍ የልኅቀት ማዕከል የተሰባሰቡ ሲሆን ዛሬ ከ4:30 ጀምሮ የመጀመርያ ልምምዳቸውን አከናውነዋል።

በዛሬው መርሐ ግብር ላይ ጥሪ ከቀረበላቸው 26 ተጫዋቾች መካከል ሃያ አራቱ የተገኙ ሲሆን ዛሬ ያልተገኙት የኤሌክትሪኮቹ እፀገነት ብዙነህ (ህመም) እና ዮርዳኖስ ምዑዝ (ስብስቡን ባለመቀላቀሏ) ናቸው። ሁለቱ ተጫዋቾችም በቀጣይ ቀናት ልምምዶች ላይ ስብስቡን በመቀላቀል እንደሚሰሩ ታውቋል።

ዘጠና ያህል ደቂቃዎች በነበረው የዛሬው ልምምድ አቋርጣ ከወጣችው ማዕድን ሳሕሉ በቀር ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ተመልክተናል። የድሬዳዋ ከተማዋ አማካይ ልምምዱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ባጋጠማት ህመም ያቋረጠች ቢሆንም አሁን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደምትገኝ ለማወቅ ችለናል።

ብሔራዊ ቡድኑ የማጣርያ ጨዋታዎችን መቼ እንደሚያርግ ባይታወቅም በመጪው ቅዳሜ እና ማክሰኞ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያከናውን ይሆናል።

የ2020 ውድድርን የሰረዘው ካፍ የ2022 ማጣርያዎች እና የዋናው ውድድር ቀን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። 12 ሀገራትን በሚያሳትፈው እና ግማሽ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ሀገራት ወደ ዓለም ዋንጫ በሚያልፉበት የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ከማጣርያው ጀምሮ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ