“ስምምነቱ የተፈፀመው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከመግባታችን በፊት ነው” – አቶ ባህሩ ጥላሁን

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትጥቅ አምራች ተቋሙ አምብሮ ጋር ያደሰውን የአራት ዓመታት የውል ስምምነት በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገለፃ አድርገዋል።

ዛሬ ከሰዓት ወሎ ሠፈር በሚገኘው ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር በተያያዘ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ዘለግ ላለ ደቂቃ በቆየው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተዋል። ከተነሱት ጉዳዮች መካከለ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ለብሔራዊ ቡድኖች ትጥቅ ከሚያቀርበው አምብሮ ጋር ያለውን የውል ስምምነት ለአራት ዓመታት ማደሱን የተመለከተው ጉዳይ አንደኛው ነው። ይህንን ጉዳይ በተመለከተም ከአሠልጣኙ ጋር መግለጫውን ሲሰጡ የነበሩት አቶ ባህሩ ጥላሁን የውል ማደሱን ሂደት በተመለከተ የሰጡት አጠር ያለ ሀሳብ የሚከተለውን ይመስላል።

“ከአምብሮ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶችን ስናደርግ ነበር። አሁን የተደረሰው ስምምነት ላይም ለመምጣት ጊዜዎች ፈጅተዋል። ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ ብሔራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ዋንጫ ባለፈ ማግስት ስምምነቱ ይፋ ሆነ። ከዚህ ጋር በተገናኘ ብዙዎች ብሔራዊ ቡድናችን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፉን ተከትሎ ስምምነቱ የተፈፀመ መስሏቸዋል። ግን ውሉ እና ስምምነቱ የተፈፀመው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከመግባታችን በፊት ነው።

“ከዚህ በፊት ከደጋፊዎች መለያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ክፍተት ነበር። ከዚህም መነሻነት አምብሮ ቅሬታዎችን እያሰማ ነበር። አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደጋፊዎችን መለያ የማቅረብ መብት አግኝቷል። ስለዚህም ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለደጋፊ የሚሆኑ መለያዎችን ከአምብሮ ይገዛል። ከዛ በኋላ ደግሞ ለሀገራችን ደጋፊዎችን መለያውን የሚሸጥ ይሆናል። በዚህ አሰራር ደግሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ አምብሮ የሚጠቀሙ ይሆናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ