የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ገላን ከተማ እና መከላከያ አሸንፈዋል፡፡ በምድብ ሐ አርባምንጭ ነጥቅ ጥሏል።
ጠዋት 3፡00 ሲል ወልዲያ እና ገላን ከተማን ያገናኘው ጨዋታ የወልድያ የጨዋታ የበላይነት ቢታይበትም ገላኖች በመልሶ ማጥቃት ያገኟቸውን ዕድሎች በአግባቡ የተጠቀሙበት ነበር። 15ኛው ደቂቃ በዚህ ሒደት ከተገኘች ኳስ ኪቲካ ጅማ ጋር ደርሳ ወደ ጎል ሲመታ ተከላካዮች በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሙሉቀን አዲሱ አስቆጥሮ ገላንን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከእረፍት መልስም ወልዲያዎች በእንቅስቃሴ የተሻሉ ቢሆኑም ገላኖችን አሸናፊ ከመሆን አላገዳቸውም። 70ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አዲሱ ከማዕዘን ሲያሻማ የቀድሞው የወልዋሎ ተከላካይ ዳዊት ወርቁ በራሱ ላይ አስቆጥሮ ጨዋታው በገላን ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
ለአንድ ቀን በኤሌክትሪክ በአንድ ነጥብ ተበልጦ የነበረው መከላከያ በዛሬው ዕለት በማሸነፍ ወደ መሪነቱ ተመልሷል፡፡ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ ረጃጅም የሆኑ ኳሶች የበዙበት የነበረ ሲሆን ዘካሪያስ ፍቅሬ ከርቀት ባደረገው ሙከራ ጦሩ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች እና ከመስመር በኩል በረጅሙ በቁመት ወደ ማይታሙት አጥቂዎች በማሻገር መከላከያዎች ጎል ለማስቆጠር ጥረዋል፡፡ 16ኛው ደቂቃ ላይም ተሳክቶላቸው ግብ አግኝተዋል፡፡ ዳዊት ማሞ ከመስመር ሲያሻማ ቴዎድሮስ ታፈሰ ኳሷ አየር ላይ እንዳለች መሬት ለመሬት አክርሮ መቶ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡
ጎል ለማስተናገድ ከተገደዱ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ደሴ ከተማዎች በቅብብል ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመጠጋት ሞክረዋል፡፡ 31ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ወርቁ መሀል ለመሀል ተሰንጥቆ የተሰጠውን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረው ሲባል ኳሷ ኢላማዋን ስታ ወጥታለች። ኳሷ ከተሳተች በኃላ የመከላከያው አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ነው በሚል በእለቱ አንደኛ ረዳት ዳኛ ላይ ሲያሰሙ የነበረው ያልተገባ ኃይለ ቃል ሊታረም እንደሚገባው ለመናገር እንወዳለን፡፡
ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማየት በቻልንበት ሁለተኛው አጋማሽ ከሙከራዎች ይልቅ በዳኛ ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎች የበዙበት ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች በርከት በማለታቸው የጠራ የግብ ሙከራን ለመመልከት ያልቻንበት ነበር፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ሳሙኤል ሳሊሶ በሳጥን ውስጥ ተጠልፎ የፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጥም አጥቂው ዘካሪያስ ፍቅሬ መቶት አንተነህ ሀብቴ አድኖበታል፡፡ ይህች የፍፁም ቅጣት ምት አግባብ አደለችም በሚልም ደሴ ከተማዎች ቅሬታን ያሰሙ ሲሆን በእለቱ ዳኛም ላይ የቴክኒክ ክስ አስይዘው ጨዋታው በቀሩት ደቂቃዎች ግብ ሳንመለከትበት ተደምድሟል፡፡
በምድብ ሐ አርባምንጭ ከተማ እና ጌዴኦ ዲላን ያገናኘውና በኮሦና ምክንያት ተሸጋሽጎ የተደረገው ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል። አላዛር ዘውዱ ዲላን በ18ኛው ደቂቃ መሪ አድርጎ ረጅም ደቂቃዎች መሪ መሆን ቢችሉም በጭማሪ ደቂቃ በድሩ ኑር ሁሴን አስቆጥሮ አርባምንጭ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እኖዲወጣ አስችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ