የቀድሞ ተጫዋች ለድሬዳዋ ስታዲየም ድጋፍ አደረገ

ነገ ከሳምንታት እረፍት በኋላ የሚጀምረው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን የሚያስተናግደው የድሬዳዋ ስታዲየም ለምሽት ጨዋታዎች ብቁ እንዲሆን ከቀድሞ ተጫዋች ድጋፍ ተደርጎለታል።

እስካሁን ከተለመደው የጨዋታ ሰዓት በተለየ ሁኔታ በምሽት ጨዋታዎችን የምታስተናግደው ድሬዳዋ ቅድመ ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። የምሽት ጨዋታዎችን በተሻለ ጥራት ሆኖም ያለምንም ጥላ ማድረግ እንዲቻል ጥረት እየተደረገ ቢቆይም በሀገር ውስጥ አስፈላጊዎቹን መብራቶች ማግኘት አለመቻሉ እና ከውጭ ሀገር እንዲመጣ ለማድረግ ደግሞ ጊዜ የሚሻማ መሆኑን ሁኔታዎችን አዳጋች አድርገውት ቆይተዋል። ይህን ሁኔታ የተረዳው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ፉአድ ኢብራሂም በራሱ ወጪ ፓውዛው ላይ የሚገጠሙና ጥላን ማስቀረት የሚችሉ LED መብራቶች ለከተማው አስተዳደር በዛሬው ዕለት አበርክቷል።

ከዚህ ቀደም ለስታዲየም መብራት በተተከሉ የብረት መዋቅሮች ላይ ለሚተከሉት ለእነዚሁ መብራቶች ገጠማ ይረዳ ዘንድ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በዛሬው እለት በአፋጣኝ እየተከናወነ ይገኛል። በነገው ዕለት ለሚደረጉ ጨዋታዎችም ዝግጁ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህም ለምሽት ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት የተሻለ ምስልን እንደሚፈጥር ታምኖበታል ።

በዚህ ድጋፍ መሠረት ሊግ ካምፓኒው ከዲኤስ ቲቪ ጋር ተመካክሮ ጨዋታዎቹ 10:00 እና ምሽት 1:00 እንዲደረጉ መወሰኑን ማሳወቁ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ