ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሰበታ ከተማ

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የድሬ ቆይታ የሚጀመርበትን ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

በመጀመሪያው ዙር በርከት ያሉ ግቦችን ካስመለከቱን ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ነገም መልካም ፉክክርን እንደሚያሳየን ይጠበቃል። ውጤቱም ውድድሩን በጥሩ መንፈስ ከመጀመር ባለፈ ጊዮርጊስን ወደ ሁለቱ ተፎካካሪዎቹ ለማቅረብ ሰበታን ደግሞ ወደ ላይኛው ፉክክር ከመግፋት አንፃር ለሁለቱም አስፈላጊነቱ ከፍ ያለ ነው።

ባህር ዳር ላይ ጥሩ ጊዜ ያላሳለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዕረፍቱ ጊዜያት ለውጦችን አስተናግዷል። አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስን ከማሰናበቱ ሌላ ሳላዲን ሰዒድ እና ፓትሪክ ማታሲን ወደ ልምምድ የመለሰው ክለቡ እንግሊዛዊው ፍራንክ ነታልን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙም አይረሳም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስምንት ቀናት ዕረፍት በኋላ ቢሾፍቱ በሚገኘው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ውስጥ ልምምዱን ሲከውን ቆይቶ ትናንት ወደ ድሬዳዋ ገብቷል። አዲሱ አሰልጣኝም ከቡድናቸው ጋር አስር የሚደርሱ ቀናትን የቆዩ ሲሆን የነገው ጨዋታ በጥቂቱም ቢሆን የእርሳቸውን የአጨዋወት ምርጫ የምናይበት እንደሚሆን ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ ግን አሰልጣኙ በአካል ብቃት ላይ ሰርተው ያለፉ እንደመሆናቸው የቡድኑ የ የዋታ ጉልበት ተሻሽሎ ሊቀርብ እንደሚችል ይገመታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው ጨዋታ ሄኖክ አዱኛ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና አዲስ ግደይን በጉዳት ምክንያት እንደማይጠቀም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ በተለየ ውድድሩ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ አስቀድሞ ጥሩ አቋም ላይ የነበሩት ባህሩ ነጋሽ እና ናትናኤል ዘለቀ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን መልካም ቆይታ የነበራቸው ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በነገው ጨዋታ የሚኖራቸው ተፅዕኖ የሚጠበቅ ይሆናል።

ሙሉ ለሙሉ ከሽንፈት የራቁበትን ጊዜ በባህር ዳር ያሳለፉት ሰበታ ከተማዎች በድሬዳዋም ተመሳሳይ ጊዜን ለማግኘት ያልማሉ። 16ኛው ሳምንት ላይ አራፊ በመሆናቸው ከሌሎች ቀድመው የቀናቻቸው ባህር ዳርን የተሰናበቱት የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ተጫዋቾች ለ15 ቀናት ያህል በዝግጅት ላይ ቆይተው ሐሙስ ዕለት የድሬዳዋን ምድር ረግጠዋል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርቦ የመንቀሳቀስ ድክመቱን ማሻሻል ችሎ የታየው ሰበታ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ግብ ማስቆጠር የቻለ ቢሆንም የፊት መስመሩን የአጨራረስ ብቃት ይበልጥ ማሻሻል ላይ እንዲሁም በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ያስተናገደው የኋላ ክፍሉን የማጠናከር ሥራ ላይ ተጠምዶ ቆይቷል። ቡድኑ ምርጫው ላደረገው ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረብ የድሬዳዋ ስታድየም መጫወቻ ሜዳ ምቹ መሆኑ ማጠራጠሩ የነገ ትልቁ ፈተናው ነው። ነገር ግን የዳዊት እስጢፋኖስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና መስዑድ መሐመድ ጥምረት ጥሩ መናበብ ላይ መገኘቱ እና የአጥቂው ፍፁም ገብረማርያም ግብ አነፍናፊነት መመለስን ካስቀጠል ከነገው ጨዋታ ውጤት ይዞ የመውጣት ዕድሉን የሚያሰፋ ይሆናል። በዕረፍቱ ጊዜ ጋናዊውን ኦሰይ ማወሊን ያስፈረሙት ሰበታዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች ታደለ መንገሻ ብቻ እንደሆነ ማወቅ ችለናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በአጠቃላይ በሊጉ ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በሁለቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች 15 ጎሎች ሲቆጠሩ አስሩን ጊዮርጊስ አምስቱን ሰበታ አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ባሕሩ ነጋሽ

ደስታ ደሙ – አስቻለው ታመነ – ምንተስኖት አዳነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ

የአብስራ ተስፋዬ – ናትናኤል ዘለቀ

አቤል ያለው – ሮቢን ንገጋላንዴ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጌታነህ ከበደ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጳውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሐመድ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ

ኦሰይ ማዊሊ – ፍፁም ገብረማርያም – ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ