ዩጋንዳዊው የተከላካይ አማካይ ተጫዋች ከሁለት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የመለሰውን ዝውውር አገባዷል።
2009 ላይ በደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደር ከነበረው ቫዝኮ ደጋማ ክለብ ጅማ አባ ቡናን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው የተከላካይ አማካዩ በጅማ ለአንድ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ወደ መዲናው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና አምርቶ እንደነበር ይታወሳል። በቡናማዎቹ ቤትም ለሁለት ዓመታት ጥሩ ግልጋሎት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን 2011 ላይ ግን ወደ ሀገሩ በመመለስ ለዋኪሶ ጂያንትስ ፊርማውን በማኖር የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ደግሞ ንታምቢ የአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ሰበታ ከተማን በይፋ ተቀላቅሏል። ንታምቢ የውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት ሳይዘጋ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ፊርማውን ያኖረ ሲሆን ነገርግን ከሀገሩ ሲመጣ በተሟላ ፍቃድ መሆን ይኖርበት ነበር። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቹ ዳግም ወደ ዩጋንዳ ተመልሶ የወረቀት ሥራዎችን አገባዶ በትናንትናው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል። ለሰበታ ከተማ ለአንድ ዓመት ግልጋሎት ለመስጠት መስማማቱ ታውቋል።
በተከላካይ አማካይ እንዲሁም በመሐል ተከላካይነት ቦታ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ክለብ ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ