ከምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ኃሳባቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
ስለታነበበት ሁለት ዓይነት ስሜት
በእርግጥ ደስ ብሎኛል ፤ ትንሽም ደግሞ ተናድጃለሁ። ምክንያቱም በቀላል ማሸነፍ በምንችለው ጨዋታ ለመሸነፍ ደርሰን ነበር። አምላክ ይመስገን ጎል አገባን ፤ ተጫዋቾቼ ብዙ ዋጋ ከፍለው። እና ደስታም ጭምር ነው። መጀመሪያ ላይ የእነሱ ግብ ጠባቂ ብዙ ኳሶችን አድኗል። አጨራረሳችን ጥሩ ቢሆን አሁን አንቸገርም ነበር ማለት ነው።
የአጨራረስ ችግር ስለመኖሩ
የመረጋጋት ችግር ነው። ልጆቹ ወጣቶች ናቸው ፤ ጉጉት አለ። ከዚህ ቀደም በጅማ በአዳማ የጣልናቸውን ነጥቦች በማየት ትኩረት አርገን ነው የመጣነው። ከእኛ በደረጃ ዝቅ ያሉ ቡድኖችን አሳንሰን በማየት እንገባለን። ትልልቅ ቡድኖችን እናሸንፋለን ፣ ነጥብ እንጋራለን። ከእንደዚህ ዓይነት ክለቦች ጋር ግን እኛ ላይ በቀላሉ ይገባብናል ለማግባት ደግሞ እንቸገራለን። ቡድናችን ጥሩ ነበር ፤ ለማግባት የነበረን ጉጉት ግን ከሚፈለገው በላይ ሆነ።
ስለውጤቱ ተገቢነት
እነሱ ካገቡ በኋላ በነበረው ነገር አዎ። እኛ ግን መጀመሪያ አግብተን የተሻለ ነገር መጨመር እንችል ነበር። ዘጠና ደቂቃ ሞልቷል አቻ መውጣታችንም ለእኛ መልካም ነገር ነው።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር
ለአቡበከር ኑሪ ስላስተላለፉት መልዕክት
ከዚህ ደቂቃ በኋላ ኳሶች በደንብ እየወጡ ከመስመር እንደሚመጡ እናውቃለን። በዚህ ላይ በግብ ጠባቂያችን አቡበከር እና በተካላካዮቻችን መሀል የነበረው ክፍተት በጣም የጠበበ ነው እና ትንሽ ነፃነት እንዲያገኙ ነው የፈለግኩት። የመሀል ተከላካዮቻችን ሸሽተው ከእርሱ ጋር ተቀራርበው ስለነበር ያ ቦታ ነፃ እንዲሆን እንዲገፋቸው ነው። ምክንያቱም በረኛ ከፊት ለፊቱ 21 ተጫዋች ይታየዋል። ስለዚህ አደጋ ከመፈጠሩ በፊት እሱ ማስያዝ መቻል አለበት። እንደሚታወቀው በጣም ወጣት ለሀገርም የሚጠቅም ግብ ጠባቂ ነው። እና ቡድኑን እንዲመራ ነበር። ያው ቀላል ሦስት ነጥብ አልነበረም ለእኛ ፤ አቻ ወጥተናል። ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው።
ከዕረፍት መልስ ስለተቀየሩ ነገሮች
ሀዋሳ ከተማ የግል ክህሎታቸው ጥሩ የሆኑ ወጣት ተጫዋቾች ያሉት ቡድን ነው።ብዙ ጊዜ አጭር ኳስ ይጫወታሉ። እኛም በእነሱ መልኩ የምንጫወት ከሆነ ብልጫ ይወስዱብናል። እኛም ረጃጅም እንዲሁም ፈጣን የመስመር አጥቂዎች አሉን። በእነሱ ለማጥቃት ነው ስታራቴጂያችንን ቀይረን የገባነው። የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ፤ በጣም ጥሩ ፉክክርም ታይቷል ብዬ አስባለሁ። ተጫዋቾቻችን የሚችሉትን አርገዋል። ዛሬ ሦስት ነጥብ ይገባን ነበር ብዬ አስባለሁ። በሁለታችን መሀል የተደረገው ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም። ዲሲፕሊኑም ጥሩ ነበር። ስለዚህ በቀጣይ ጨዋታ የተሻለ ተዘጋጅተን ለመቅረብ ነው የምናስበው
© ሶከር ኢትዮጵያ