ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በድሬዳዋ ከተማ የተደረገው የመጀመሪያው የ17ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ከሦስት ሳምንት በላይ የእረፍት ጊዜ የነበረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የአራተኛ ከተማ ቆይታውን በይፋ ጀምሯል። በጨዋታውም ሁለቱም ቡድኖች በባህር ዳር ከነበራቸው የመጨረሻ ጨዋታ ለውጦችንን አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል። በአዲሱ አሠልጣኝ ፍራንክ ነታል የሚመሩት ፈረሰኞቹም ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጨረሻ ጨዋታ ሄኖክ አዱኛ፣ አብዱልከሪም መሀመድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ጋዲሳ መብራቴን በምንተስኖት አዳነ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ፣ ሙሉአለም መስፍን እና አቤል ያለው ተክተዋል። ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በ15ኛ ሳምንት ሀዋሳን ገጥመው ካሸነፉበት ጨዋታ ቃልኪዳን ዘላለምን በአዲሱ አጥቂያቸው ኦሰይ ማወሊ ብቻ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።


ኳስን በተሻለ ተቆጣጥረው ጨዋታውን የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በአምስተኛው ደቂቃ ሰንዝረዋል። በዚህም በቀኝ መስመር የተገኘውን ኳስ ኦሴ ማውሊ ለመስዑድ መሐመድ አቀብሎት መስዑድ ጥሩ ጥቃት ፈፅሟል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጣሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከደቂቃ በኋላ በጌታነህ ከበደ የርቀት ኳስ የሰበታን ግብ መፈተሽ ጀምረዋል። ከሰከንዶች በኋላም የሰበታው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሎ ከተከላካዮች የተቀበለውን ኳስ ለማውጣት ሲጥር አቤል ያለው ደርሶ ኳሱን በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ ነበር።
በጥሩ ፍክክር የጀመረው ይህ ጨዋታ አሁንም የግብ ማስቆጠር ሙከራዎችን ማስተናገድ ቀጥሏል። በስምንተኛው ደቂቃም ዳዊት እስቲፋኖስ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ልኮት ባህሩ በሚገርም ቅልጥፍና አምክኖታል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ጊዮርጊሶች በፈጣን ሽግግር ወደ ሰበታ የግብ ክልል ደርሰው በአቤል አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል።

በአንፃራዊነት ለግብነት የቀረቡ ግልፅ ሙከራዎችን በማድረግ ተሽለው የታዩት ሰበታዎች በ24ኛው ደቂቃ እጅግ ወደ ጎል ተጠግተው ነበር። በዚህ ደቂቃም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ለቆት የወጣውን ቦታ በመጠቀም ፈጣን ሩጫ ያደረገው ማውሊ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ባህሩ መልሶበታል። በተቃራኒው በአመዛኙ ፈጣን ሽግግሮችን እና ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በተጠቀሰው የእንቅስቃሴ መንገድ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በዚህም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ያገኘው አቤል አጋጣሚውን ወደ ግብነት ይቀይረዋል ተብሎ ቢጠበቅም ተጫዋቹ በወረደ አጨራረስ ዕድሉን አምክኖታል። ምርጥ ፉክክር ያሳየው የመጀመሪያው አጋማሽ በመገባደጃው ላይም ያለቀለት የግብ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም በ42ኛው ደቂቃ ማውሊ እንዲሁም በ45+3ኛው ደቂቃ ጌታነህ ለየቡድኖቻቸው ሙከራ አድርገዋል። አጋማሹ እጅግ አዝናኝ እና በድምሩ 17 ሙከራዎች የተስተናገዱበት ቢሆንም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የሁለተኛውም አጋማሽ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃራዊ የማጥቃት ሀይላቸውን ተሽሎ መታየት ጀምሯል። በተለይም ቡድኑ በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ባገኛቸው ሁለት የቅጣት ምቶች ግብ ለማስቆጠር ሞክሯል። በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያጡት ሰበታዎች በዚህኛው አጋማሽ በራሳቸው የግብ ክልል ተገድበው ሲጫወቱ ተስተውሏል።

ጨዋታው ቀጥሎም በዚህኛው አጋማሽ እጅግ ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ፈረሰኞቹ በ66ኛው ደቂቃ መሪ ሊሆኑበት የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህ ደቂቃም ሀይደር ሸረፋ በግል ጥረቱ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ልኮት ምንተስኖት መልሶታል። የተመለሰውንም ኳስ የቡድኑ አምበል ጌታነህ አግኝቶት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር። እነዚህ ሙከራዎች ከተደረጉ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ከነዓን ማርክነዕ ከተከላካዮች መሐል ሮጦ በመውጣት ያገኘውን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል።

አብዛኛውን የአጋማሹን ደቂቃ በመከላከሉ ላይ ያሳለፉት ሰበታዎች የሁለተኛውን አጋማሽ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ያደረጉት በ83ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም የፍፁምን መቀየር ተከትሎ የመሐል አጥቂ የሆነው ማውሊ ጥብቅ ኳስ ወደ ግብ ልኮ ባህሩ አድኖበታል። ከደቂቃ በኋላም ተቀይሮ የገባው ፎአድ ፈረጃ እጅግ አስቆጪ ዕድል አምክኗል። 10 ሰዓት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርካታ ሙከራዎችን ያስተናገደ ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከተሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን 27 በማድረስ ያሉበት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሰበታዎችም የሰበሰቧቸውን ነጥቦች 19 በማድረስ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ