ሪፖርት | ሀዋሳ በድጋሚ ከቡና ሦስት ነጥብ ወስዷል

ምሽቱን በተከናውነው የ17ኛው ሳምንት የሊጉ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡና ከድሬዳዋው ድል ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በታፈሰ ሰለሞን ብቻ በመቀየር ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ ሀዋሳ ከተማ በሰበታ ከተማ ሲሸነፍ ከተጠቀመበት ቡድን ውስጥ ባደረጋቸው ሦስት ለዉጦች ብርሀኑ በቀለ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ተባረክ ሄፋሞን በአለልኝ አዘነ ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና መስፍን ታፈሰ ቦታ መተካትን መርጧል።

ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የጨዋታው ቀዳሚ አጋማሽ አደገኛ ሙከራዎችን እምብዛም አላሳየንም። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታውን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ማቆየት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በቀጥተኛ አጨዋወት በተደጋጋሚ በቡና የግብ ክልል መገኘት ሲችሉ ታይተዋል። ኤፍሬም ዘካርያስ 3ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ የወጣበት እንዲሁም 10ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ከቅርብ ርቀት አክርሮ መትቶት አቤል ማሞ በአስገራሚ ሁኔታ ያዳነው ኳስም ቡድኑ ለወሰደው ብልጫ ማስረጃ መሆን ይችላል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ሀዋሳዎች በሙከራቸው መቀጠል ባይችሉም ቡና ከግብ ክልሉ ኳስ በቀላሉ እንዳይጀምር በማድረግ ከፍ ባለ ትኩረት ለማፈን ችለው ታይተነበር።

በተወሰኑ አጋጣሚዎች ስኬታማ ቅብብሎችን ከውነው መሀል ሜዳውን ለማለፍ የቻሉት ቡናዎች የተጋጣሚያቸው ጫና ቀለል እያለ በሄደባቸው የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በንፅፅር ተሽለው ታይተዋል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉንም ተሳላፊዎቻቸውን በሀዋሳ ሜዳ ላይ በማስገባት ክፍተት ለመማጋኘት ያጣሩባቸው ቅፅበቶች ባይጠፉም ወደ ሳጥኑ ዘልቆ መግባት እጅግ አስቸግሯቸው ታይተዋል። ይልቁኑም አልፎ አልፎ ሀዋሳዎች የተሻለ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሙዎችን ማግኘት ሲችሉ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ በኩል በኤፍሬም ዘካርያስ ያደረጉት አደገኛ ሙከራ ግብ ከመሆን የዳነውም በአቤል ማሞ ልዩ ጥረት ነበር።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ወደ ጨዋታው መንፈስ ባልገቡባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ወደ አደገኛ የግብ ዕድልነት የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በሂደት ትኩረታቸውን መልሰው ሲያገኙ ግን እንቅስቃሴው ወደ ቀደመው ሁኔታው ተመልሷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያውም የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን ይዘው በቀኝ መስመር አጥቂው ሚኪያስ መኮንን በኩል ባመዘነ የማጥቃት ሂደት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል። ያም ቢሆን የሀዋሳ ከተማ የመከላከል አደረጃጀት ጥብቅ ሆኖ አምሽቶ ሶሆሆ ሜንሳህን ከከባድ ሙከራዎች መጠበቅ ችሏል።

ጨዋታው በዚህ ሁኔታ በቀጠለበት ሂደት ከሁለተኛው አጋማሽ የውሀ ዕረፍት በኋላ ከቀኝ መስመር ካደላ ቅጣት ምት መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን የተላከችው የኤፍሬም ዘካርያስ ኳስ ልዩነት ፈጥራለች። ኳሷን ግዙፉ ተከላካይ ምኞት ደበበ ጨርፎ ወደ ግብነት መቀየር የቻለ ሲሆን ግቧም ሀዋሳ ከተማን ወሳኝ ሦስት ነጥቦች ያስጨበጠች ነበረች። ቡናዎች በጨዋታው ማብቂያ ደቂቃዎችም ጥረታቸውን ቢቀጥሉም ከአቡበከር ናስር የመጨረሻ ደቂቃ ኢላማውን ያልጠበቀ መከራ ውጪ ሌላ ዕድል ሳይፈጥሩ በከፍተኛ እልህ እና ጉሽሚያ የዘለቀው ጨዋታ ፍፃሜውን አግኝቷል።



© ሶከር ኢትዮጵያ