የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ሀዋሳ ከተማ

የምሽቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

በጨዋታው ያሰቡትን እንቅስቃሴ ስላለመከወናቸው

ሀዋሳዎች የአማካይ ሦስተኛ ሜዳ ላይ ነው እንቅስቃሴውን ማቆም የፈለጉት ፤ በአራት ሰው የእኛን አምስት ሰው ለመቆጣጠር ነው የፈለጉት። ነገር ግን ይህን ሲያደርጉ አንደኛውን ሰው እየተዉ ኳሱ በሚሄድበት መስመር በኩል አጥብበው ኳስ ለመንጠቅ ነው ያሰቡት። ከዕረፍት በኋላ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ባደረግነው ጥረት በተለይም መስመር ላይ ያሰብነውን ክፍተት አግኝተናል። ከኋላ አራት የማይንቀሳቀሱ ተጫዋቾች ስላሏቸው ወደ ውስጥ ለመግባት እዛ ጋር ነበር የመጀመርያውን ስራ መስራት የነበረብን። ቦታዎቹን አግኝተን የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ያለውን ነገር በተገቢው መንገድ መስራት አልቻልንም። ብዙ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻልንም።

ጉሽሚያዎች መበርከታቸው ስለነበረው ተፅዕኖ

ዳኞች የእኛን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተጫዋቾች መከላከል አለባቸው ፤ ህጉን ተግባራዊ በማድረግ። ካልሆነ ግን ተጫዋቾች በነፃነት መጫወት አይችሉም። በስጋት መጫወታቸው ደግሞ ያላቸውን አቅም እንዳያሳዩ ያደርጋቸዋል። በሙሉ ልባቸውም ኳሱ ላይ መስራት ያለባቸውን እንዳይሰሩ ያደርጋል። ከዚያ ደግሞ ሁኔታው ሲቀጥል ወደ ስሜታዊነት ይወስዳቸዋል። እርግጥ ነው ዳኞች ጋር ስህተት ሲኖር ተጫዋቾች ስሜታዊ መሆን አለባቸው የሚለው ባያስኬድም በተደጋጋሚ ጥፋት ሲሰራባቸው ወደእንደዛ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የመግባት ነገር ነበር።

እስከመጨረሻው ቅያሬዎችን ስላለማድረጋቸው

ተጫዋቾቹ በተቻለ መጠን የምንላቸውን እያደረጉ ነበር። ቅድም እንዳልኩት አማካይ ሦስተኛ ሜዳ ላይ ክፍተት ለማግኘት ነበር የሞከርነው። እነሱ ለመተካካት ፍጥነታቸው ዝግ ይል ስለነበር አንድ መስራት የፈለግነው ነገር ነበር። ግን በእነሱ መዘግየት ውስጥ በነበረው ክፍተት ለመጠቀም እኛም ዘግይተን ነበር። አጠቃላይ የእንቅስቃሴው ችግር ነበር። ለዛ ነው ቅያር ላይ ያላተኮርነው።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ከጨዋታው ዕቅድ አንፃር የቡድኑ እንቅስቃሴ ሲመዘን

መጀመሪያ ብዙ ተጫዋቾች ጉዳት ላይ ነበሩብን። የተሟላ ቡድን አልነበረንም። ቢሆንም ግን ባሉት ተጫዋቾች ተጠቅመን ካለንበት ደረጃ አንፃር ውጤቱ የግድ ስለሚያስፈልገን ሙሉ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ነበር ዕቅዳችን እሱንም አሳክተናል።

ዕቅዳቸው በተጋጣሚ አቀራረብ ላይ መነሻውን ስለማድረጉ

ሊጉ ላይ እንደ ኢትዮጵያ ቡና እና ሰበታ ከተማ ዓይነት ቡድኖች ክፍተት እና ጊዜ ከሰጠህ የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉ ሊያደርጉ ይችላሉ። እኛ ደግሞ ውጤቱ ስለሚያስፈልገን በእነሱ ክፍተት ገብተን ለማስቆጠር ነበር ሀሳባችን። ያንንም አድርገነው ውጤታማ መሆን ችለናል።

ተጫዋችች ላይ ይታይ ስለነበረው ስሜታዊነት

ከመጀመሪያም ጀምሮ የመጣ ነው። የተጎዱብን ተጫዋቾች ስለነበሩ ያሉትን ሁሉም ለእኔ እኩል እንደሆኑ እና ማናቸውም መጫወት እንደሚችሉ ኃላፊነቱንም እንደምወስድላቸው ስለነገርኳቸው ጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ ነበርን። መነሳሳቱ ከዛ የጀመረ ሲሆን ሜዳ ውስጥም በተግባር የታየው ይሄ ነበር።


© ሶከር ኢትዮጵያ