በፊፋ ወርሐዊ የሀገራት ደረጃ ኢትዮጵያ መሻሻሎችን አስመዝግባለች

የዓለም እግር ኳስ የበላይ የሆነው ፊፋ የወቅታዊውን የሀገራት ደረጃ ሲያወጣ ኢትዮጵያ የደረጃ መሻሻሎችን ማስመዝገቧ ታይቷል።

የሀገራትን የእግር ኳስ ደረጃ በየወሩ የሚያወጣው ፊፋ ትላንት አመሻሽም የመጋቢት ወርን የሀገራት ደረጃ በድህረ-ገፁ ይፋ አድርጓል። ለበርካታ ወራት የዓለም እግር ኳስ ቁንጮ ሆና የዘለቀችው ቤልጂየም አሁንም በ1783.38 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ቤልጂየምን በመከተል ፈረንሳይ፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ እና ፖርቱጋል ከሁለት እስከ አምስት ያለውም ቦታ ባለመልቀቅ አውራነታቸውን አስቀጥለዋል።

ከባለፈው ወር በዩኤስኤ እና ሲውድን ተበልጣ ከዓለም 22ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ሴኔጋል ከአህጉራችን ሀገራት ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። ከሴኔጋል ቀጥሎ ቱኒዚያ ከዓለም 26ኛ ከአፍሪካ 2ኛ፣ ናይጄሪያ ከዓለም 32ኛ ከአፍሪካ 3ኛ፣ አልጄሪያ ከዓለም 33ኛ ከአፍሪካ 4ኛ እንዲሁም ሞሮኮ ከዓለም 34ኛ ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በየካቲት ወር አጋማሽ በወጣው የጥር ወር የሀገራት ደረጃ ላይ በ1066 ነጥቦች 146ኛ ደረጃን ይዛ የነበረችው ኢትዮጵያ በዚህኛው ወር በወጣው ዝርዝር ስድስት ደረጃዎችንን አሻሽላለች። በዚህም በ1079.41 ነጥቦች 140ኛ ደረጃን ላይ ተቀምጣለች። በአህጉራችን አፍሪካ ከሚገኙ 54 ሀገራት ደግሞ 14 ሀገራትን በልጣ 40ኛ ደረጃን (ከባለፈው ወር አንድ ደረጃን አሻሽላለች) ይዛለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ