ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀው የነገ ምሽቱን የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማን ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
ሽንፈት ካስተናገዱ ሰባት ጨዋታዎች ያለፋቸው ወላይታ ድቻዎች (በስምንተኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0) አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ወደ ቡድናቸው ካመጡ በኋላ ያሳዩትን መነቃቃት ለማስቀጠል እና በሊጉ ደረጃ ሠንጠረዥ አናት ከሚገኙ ክለቦች ጋር ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ ሦስት ነጥብን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በተቃራኒው በዘንድሮ የውድድር ዘመን ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ወደ ዋንጫ እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ለማፋጠን እና አስራ አራተኛ ተከታታይ ያለመሸነፍ ሪከርዱን ለማስመዝገብ ጠንክሮ ለጨዋታው እንደሚቀርብ ይገመታል።
አዲስ አሠልጣኝ ከሾሙ በኋላ አልቀመስ ያሉት ወላይታ ድቻዎች ድሬዳዋ ላይ ለሚደረገው የአራተኛ ምዕራፍ የሊጉ ጨዋታዎች ዝግጅት የጀመሩት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር። ቡድኑ ሶዶ ላይ ለጥቂት ቀናት ከተለማመደ በኋላም ከአስር ቀን በፊት ወደ ድሬዳዋ በመምጣት መደበኛ ዝግጅቱን ማድረግ ቀጥሏል። በውድድሩ አጋማሽ በነበረው የዝውውር መስኮት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ቡድኑም በዝግጅት ጊዜው በዋናነት የውህደት ስራዎችን እንደሰራ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም የማጥቃት ሂደቱ ላይ ያተኮሩ ልምምዶችን ሲከውን እንደነበር ተገልጿል።
ምንም እንኳን ቡድኑ ጠንካራ የዝግጅት ጊዜን አሳልፎ የድሬዳዋን ውድድር ቢጠባበቅም ትናንት እና ዛሬ የተሰሙት መጥፎ ዜናዎች ቡድኑ ላይ መጥፎ ጥላን እንዳያጠሉ አስግቷል። ይህም አሠልጣኝ ዘላለም በአጠቃላይ ስምንት በቋሚነት ከሚጫወቱ ደግሞ ሰባት ተጫዋቾችን በነገው ዕለት በህመም ምክንያት የማያገኙ ይሆናል። በዚህም በቋሚነት ጨዋታውን እንደሚጀምሩ የሚጠበቁት አንተነህ ጉግሳ፣ ደጉ ደበበ፣ ነፃነት ገብረመድህን፣ በረከት ወልዴ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ኢዙ አዙካ እና ፀጋዬ ብርሃኑ ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል። ይህንን ተከትሎም ቡድኑ እጅግ ሳስቶ ለጨዋታው እንዳይቀርብ አስግቷል። ከሰባቱ ቋሚ ተጫዋቾች በተጨማሪም መሳይ ኒኮል በተመሳሳይ ህመም ምክንያት ለጨዋታው ዝግጁ እንዳልሆነ ተገልጿል።
ለአስራ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት የማያቁት (በሁለተኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 3-1) ፋሲል ከነማዎች እጅግ ለዋንጫው እየቀረቡ ነው። በአንፃራዊነት ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦች በተሻለ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ጠንካራ እና ወጥ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን የሰበሰበው ቡድኑ ባህር ዳር ላይ የሦስተኛ ምዕራፍ የሊጉ ጨዋታዎች ከተገባደደ ከአንድ ሳምንት በኋላ በእዛው ባህር ዳር መቀመጫውን በማድረግ ዝግጅቱን ሲያደርግ ነበር። እርግጥ ቡድኑ ስድስት ወሳኝ ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ አሳልፎ በመስጠቱ የተሟላ የህብረት ዝግጅት ባያደርግም የተጫዋቾች ብቃት ተጠብቆ እንዲቀጥል የሚያደርግ ልምምድ ላይ አትኩሮት በመስጠት ስራዎችን ሲሰራ መክረሙ ተነግሯል።
ከአብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ዘግየት ብሎ (ትናንት) ድሬዳዋን የረገጠው ፋሲል ከነማ የምስራቂቷን ከተማ ለየት ያለ የአየር ፀባይ ለመልመድ እንዳይቸግር አስግቷል። በተለይ የነገ ተጋጣሚው ድቻ ቀደም ብሎ ድሬ መድረሱ እና የከተማውን የአየር ሁኔታ በአንፃራዊነት መለማመዱ ሲታሰብ ፋሲል በዚህ ረገድ እንዳይጎዳ ያሳስባል። ምንም ቢሆን ምንም ግን በደረጃ ሠንጠረዡ የሚከተሉት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ነጥብ መጣላቸው ለቡድኑ መልካም ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሚሆን ይታሰባል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ7 ጊዜያት ሲገናኙ አቻ በማያውቀው ግንኙነታቸው ተመጣጣኝ ሪከርድ አላቸው። በውጤታቸው ፋሲል አራት ድቻ ደግሞ ሦስት ጊዜ ባለድል ሲሆኑ ዕኩል ዘጠኝ ግቦችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-2-3-1)
ዳንኤል አጃይ
አናጋው ባደግ – ዮናስ ግርማይ – መልካሙ ቦጋለ – ያሬድ ዳዊት
መሳይ አገኘሁ – አበባየሁ አንጪሶ
ዲዲዬ ሌብሪ – እንድሪስ ሰዒድ – ቸርነት ጉግሳ
ስንታየሁ መንግሥቱ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኪ
እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ሀብታሙ ተከስተ
በረከት ደስታ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ
ሙጂብ ቃሲም
© ሶከር ኢትዮጵያ