በእዳ ምክንያት ችግር ላይ የሚገኙት ተጫዋቾች…

በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ በምድብ ስድስት ተደልድሎ እየተጫወተ የሚገኘው የነገሌ ቦረና እግር ኳስ ተጫዋቾች በእዳ ተይዘው ለችግር ተዳርገዋል፡፡

በሻሸመኔ ከተማ እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የምድብ ስድስት ተወዳዳሪ የሆነው ነገሌ ቦረና ባስመዘገባቸው ደካማ ውጤቶች ከአስር የምድቡ ቡድኖች ግርጌውን እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ከውጤቱ ባሻገር ቡድኑ የደሞዝ አለመከፈል እና ባልተከፈሉ እዳዎች ምክንያት መቸገራቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

” የስምንት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም። ሁሉም ይሄ ችግር ሲመጣ ጥሎን ጠፍቷል። በዚህም መነሻነት በያዘነው ሆቴል ውስጥ ከአስራ አምስት ቀን በላይ የአልጋ እና የምግብ ክፍያ ባለመክፈላችን በእዳ ተይዘን እንገኛለን። ቤተሰብ ከእኛ አንድ ነገር አገኛለሁ ብሎ ሲያስብ ኪሳችን ባዶ ሆኖ የምንመገበው አጥተናል። አዕምሮአችንም በጣም ተጎድቷል። ለክለቡ አመራሮች በተደጋጋሚ ደውለን እንዲከፍሉ ብንጠይቅም ማንም ዞር ብሎ ሊመለከተን አልቻለም። ‘የራሳችሁ ጉዳይ’ እስከማለትም ደርሰዋል።” ሲሉ በእንባ ገልፀውልናል፡፡

ንብረታቸው እና ሻንጣቸው በእዳ የተያዘባቸው ተጫዋቾች በአሁኑ ሰዓት ከቡድን መሪ ውጪ አጠገባቸው ማንም አካል እንደሌለ የተመለከትን ሲሆን የሚበሉት በማጣታቸው የምድብ ስድስት ሰብሳቢው መሪ አቶ መሐመድ ለተጫዋቾቹ የሚበሉበትን ገንዘብ ጭምር ሲሰጡ ተመልክተናል። ይሄ ችግር ከምን የመጣ ነው በሚል ለነገሌ ቦረና ከተማ ከንቲባ አቶ በቀለ ደውለን የተፈጠረውን ችግር እንዲህ ብለው መልስ ሰጥተውናል። “በእርግጥ የተጫዋቹን ችግር እረዳለሁ። ይሄ ክፍተት የመጣው በገንዘብ እጥረት የተነሳ ነው፡፡ እኔ ይሄን ችግር በሰማሁ ሰዓት ገንዘብ እንዲከፈላቸው ፈርሜ ለክለቡ የበላይ አካላት ሰጥቻለሁ። እንደውም በግሌ ተጨማሪ በጀት እንዲሰጣቸው ለማድረግ ሥራ ጀምሬያለሁ። እኔ ይሄ ችግር ሲፈጠር ለአስራ ስድስት ቀን ስብሰባ ላይ ነበርኩ። ገና አሁን ወደ ሥራ ስገባ ነው ይሄን የሰማሁት። ስለዚህ በአጭር ጊዜ ቅሬታቸውን እንፈታለን ብዬ እገምታለሁ።” ብለዋል።

ዛሬ በሚጠናቀቀው የምድብ ስድስት ጨዋታ ላይ ቡድኑ አሰልጣኝን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ባለመኖራቸው ለሦስተኛ ጊዜ ለተጋጣሚ ቡድን የፎርፌ ውጤት ለመስጠት እንደሚገደድ በተጨማሪም የበላይ አመራሮች ዛሬ ነገ ከማለት ውጪ ይከፍሉናል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተጫዋቾቹ ገልፀውልናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ