የዲኤስ ቲቪ የምሽት ጨዋታዎች ቀጥታ ስርጭት ጉዳይ ከምን ደረሰ?

ምሽት አንድ ሰዓት ላይ የሚደረጉ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የማግኘታቸውን ጉዳይ በተመለከተ አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስያሜውን ለቤትኪንግ የቴሌቪዥን መብቱን ደግሞ ለሱፐር ስፖርት ሸጦ በተለየ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል። የሊጉ የበላይ አካል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከውድድር ዓመቱ መጀመር በፊት 60 ጨዋታዎችን ለስፖርት ቤተሰቡ ለማድረስ ከሱፐር ስፖርት ጋር ስምምነት ፈፅሞ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሱፐር ስፖርት ከሁለት ያልበለጡ ጨዋታዎችን ብቻ የቀጥታ ሽፋን ሳይሰጣቸው በአጠቃላይ ከስምምነቱ እጅግ የላቀ ጨዋታዎችን በቀጥታ ሲያስተላልፍ ነበር።

ይህ ሂደት ድሬዳዋ በሚኖረው ቆይታም ይቀጥላል ቢባልም በከተማው ባለው ሙቀት መነሻነት የጨዋታ ሰዓቶች ወደ ምሽት መተላለፋቸውን የቀጥታ ስርጭቱ ላይ መስተጓጎል አምጥቷል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በስዲየሙ የተተከሉት የብርሃን ፓውዛዎች በቂ አለመሆናቸው ነው። ይህንን ተከትሎም ፓውዛዎቹን ዝግጁ የማድረግ ሥራዎች ዘግይተው በመከናወናቸው ትላንት ምሽት የተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ሳያገኝ ቀርቷል።

ትናንት እና ከትናንት በስትያም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች በፓውዛዎቹ ላይ እንዲከወኑ አድርጎ ጥሩ ውጤት የተገኘ ይመስላል። የቀጥታ ስርጭት ያላገኘው የትናንት ምሽቱም ጨዋታ ተቀርፆ እንደነበረ እና ደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ከፍተኛ የቴክኒክ ክፍሎች እንደተላከ ተሰምቷል። ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ደግሞ በስታዲየሙ ላይ የተደረገው የብርሃን መሻሻል ጥሩ መሆኑ እና ድሬዳዋ የሚገኘው የሱፐር ስፖርት ልዑካንን ደስተኛ እንዳደረገ ተገልጿል። ከዚህም መነሻነት ከሰዓታት በኋላ ከደቡብ አፍሪካ የሚመጣው መልዕክት የተለየ እስካልሆነ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ የሚደረጉ የምሽት ጨዋታዎች በቀጥታ እንደሚተላለፉ ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ