ሪፖርት | ዐፄዎቹ ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ አፋጥነዋል

ዐፄዎቹን እና የጦና ንቦቹን ያገናኘው የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ በፋሲል ከነማ ሁለት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

በህመም ምክንያት አስገዳጅ ለውጦችን ለማድረግ የተገደዱት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በ16ኛ ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ መክብብ ደገፉ፣ ደጉ ደበበ፣ አንተነህ ጉግሳ፣ ጋቶች ፓኖም፣ በረከት ወልዴ እና ፀጋዬ ብርሀኑን በዳንኤል አጄዬ፣ ዮናስ ግርማይ፣ መልካሙ ቦጋለ፣ አበባየሁ አጪሶ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ቢኒያም ፍቅሩ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ አሠልጣኝ ስዩም ከበደ ጅማ አባ ጅፋርን ከረቱበት የመጨረሻ ቋሚ ስብስብ ይሁን እንዳሻውን ብቻ በሀብታሙ ተከስተን ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

ገና ጨዋታው በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ተጋጣሚ ላይ ጥቃት የሰነዘሩት ፋሲል ከነማዎች በረከት ደስታ በግራ መስመር ከተከላካይ ጀርባ ሮጦ ወደ ጎል በመታው ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተቃራኒው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በራሳቸው በኩል እጅግ ጥሩ አጋጣሚ ያገኙት ወላይታ ድቻዎች የጨዋታውን ቀዳሚ ጎል ከመረብ ለማገናኘት ሞክረዋል። በዚህም በአምስተኛ ደቂቃ የፋሲል ከነማ ተጨዋቾችን ተጭነው የተቀበሉትን ኳስ ስንታየሁ መንግስቱ ለቢንያም ፍቅሬ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶለት የነበረ ቢሆንም የፋሲሉ የግብ ዘብ ሜኬል ሳማኪ ሰውነቱን አግዝፎ ከክልሉ በመውጣት ዕድሉን አምክኖታል።

ከሁለቱ የመጀመሪያ ደቂቃ ሙከራዎች በኋላ ዘለግ ላለ ደቂቃ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ያላስመለከተው ጨዋታው ፋሲል ከነማን በእንቅስቃሴ የበላይ ያደረገ ነበር። ቡድኑም የወሰደውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በጎሎች ለማጀብ ቀጣይ ሙከራውን ያደረገው በ32ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ቡድኑ ያደረገው ጥቃት ፍሬ አፍርቶ ሙጂብ ቃሲም ከእንየው ካሳሁን የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ወደ ጎልነት ቀይሮ መሪ ሆኗል።

በአንፃሩ በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ጨዋታውን እየቀጠሉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች የፋሲል ከነማን የማጥቃት ሂደት እያቋረጡ የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ ወደ ፊት በመላክ የአቻነት ጎል ፍለጋቸውን ጀምረዋል። ግብ ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ዲዲዬ ለብሪ ከርቀት ዳንኤል አጃዬ የላከለትን ኳስ በግብ ጠባቂው ሳማኪ አናት በመላክ ግብ ለማስቆጠር የሞከረ ቢሆንም ከድር ኩሊባሊ በፍጥነት ሳማኪ ትቶት የሄደው ቦታ ላይ በመገኘት ኳሱን አውጥቶታል። ቀሪው የአጋማሹ ደቂቃም ምንም የግብ ማግባት ሙከራ ሳይስተዋልበት ተጫዋቾች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉትን ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ ግብነት ቀይረው መሪ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በዚህኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታን የመቆጣጠሩ ሂደት ላይ አተኩረው ሲጫወቱ ታይቷል። በአንፃሩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ግብ የሚያስፈልጋቸው ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ስንታየሁን ዒላማ ያደረጉ ኳሶችን በተደጋጋሚ በመላክ የፋሲል የግብ ክልል መጎብኘት ይዘዋል። በ58ኛው ደቂቃም ቢንያም ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ቁመተ መለሎው አጥቂ ስንታየሁ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ሳማኪ አምክኖበታል።

ያስቆጠሩት አንድ ጎል የበቃቸው የሚመስለው ፋሲሎች የጨዋታውን ሁለተኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በራሳቸው በኩል ያደረጉት በ69ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ከደቂቃ በፊት በረከትን ለውጦ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሙጂብ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ አጃይ አድኖበታል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ግን የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል። ተጫዋቹም ከሽመክት ጉግሳ የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ዳንኤል አጄይ መረብ ላይ አሳርፎታለል።

የመጨረሻ ሀይላቸውን አሟጠው በመጠቀም ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረታቸውን የቀጠሉት ድቻዎች በ85ኛው ደቂቃ አስቆጪ ዕድል አምክነዋል። በዚህም ስንታየሁ ለቢንያም እጅግ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት የነበረ ቢሆንም ቢንያም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም በ89ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ዲዲዬ ለብሪ ለስንታየሁ በደረቱ አመቻችቶለት ስንታየሁ ኳሱን ወደ ግብነት ሳይለውጠው ቀርቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት ፋሲል ከነማን 2-0 በሆነ ውጤት አሸናፊ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች በ21 ነጥቦች ባሉበት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል። ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ወደ 14 ያሳደጉት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 በማሳደግ ወደ ዋንጫው የሚያደርጉተን ጉዞ አጠናክረው ቀጥለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ