ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ተወሰነ

ከ10 የማይበልጡ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ፈቅዶ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በኮቪድ-19 ምክንያት ክልከላ ጥሏል።

እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጊዜያት በስፖርት ቤተሰብ ታጅቦ እየተከናወነ የማይገኘው የዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ምዕራፍ ውድድሩን በትናንትናው ዕለት በድሬዳዋ ጀምሯል። ገና ከጅምሩ ችግር ያላጣው የድሬዳዋ ቆይታው ከኮቪድ-19 ስርጭት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አደጋ ከፊቱ ተጋርጦበታል።

ይህንን ተከትሎም የሊጉ የበላይ አክሲዮን ማኅበሩ ከሰዓታት በፊት የሁሉም ክለብ የቡድን መሪዎችን ሰብስቦ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል። በስብሰባው ላይም አሁን ያለውን ወቅታዊ የኮቪድ ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት ተፈቅዶላቸው የነበሩ የየክለቦቹ 10 ደጋፊዎች ላልተወሰነ ጊዙ ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ መወሰኑ ታውቋል። ከደቂቃዎች በፊት የተላለፈው ውሳኔም ለየክለቦቹ እንደተላከ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ