የቤትኪንግ የምሽት ጨዋታዎች በቀጥታ የመተላለፋቸው ነገር እርግጥ ሆኗል

አሁን በወጣ መረጃ በድሬዳዋ የሚደረጉት የምሽት ጨዋታዎች በቀጥታ እንደሚተላለፉ ማረጋገጫ ተሰጥቶባቸዋል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የቴሌቪዥን መብት የገዛው ሱፐር ስፖርት በአዲስ አበባ፣ ጅማ እና ባህር ዳር የተደረጉ 95 ጨዋታዎችን በቀጥታ ሲያስተላልፍ መዝለቁ ይታወቃል። ሊጉ ትናንት የ17ኛ ሳምንት ጨዋታውን በድሬዳዋ ሲጀምርም ሱፐር ስፖርት የ10 ሰዓቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሰበታ ከተማ መርሐ-ግብር በቀጥታ አስተላልፏል። ይሁን እና በድሬዳዋ ስታዲየም የተገጠሙትን የመብራት ፓውዛዎች አቅም ለመገምገም የምሽቱ የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በቀጥታ ሳይተላለፍ ቀርቶ ነበር።

ጨዋታውን በቀጥታ የሚያስተላልፈው እና ድሬዳዋ የሚገኘው የሱፐር ስፖርት ልዑካንም ትናንት ምሽት በተደረገው ሙከራ ውጤት ደስተኛ መሆኑ ሲገለፅ ነበር። ረፋድ ላይ ባስነበብነው ዘገባም ከዛሬ ጀምሮ የሚደረጉት የምሽት ጨዋታዎች የመተላለፋቸው ውሳኔ ከደቡብ አፍሪካ እንደሚተላለፍ ገልፀን ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረትም ከደቡብ አፍሪካ አዎንታዊ ምላሽ በመምጣቱ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ከሚያደርጉት የዛሬ ምሽት ጨዋታ ጀምሮ የድሬዳዋ የምሽት አንድ ሰዓት መርሐ-ግብሮች በቀጥታ ይተላለፋሉ።

*ትናንት ምሽት የተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በአሁኑ ሰዓት በቫራይቲ 3 እየታየ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ