በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ያጠላውን ኮቪድ-19 በተመለከተ ምክክር ሊደረግ ነው

በድሬዳዋ ከተማ እየተደረገ ባለው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከፍተኛ ችግር የሆነው የኮቪድ-19 ጉዳይን በተመለከተ ምክክር ሊደረግ መሆኑ ታውቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት እየተደረገ የሚገኘው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አበባ፣ ጅማ እና ባህር ዳር የ16 ሳምንታት ቆይታን ካደረገ በኋላ በትናንትናው ዕለት የአራተኛ ምዕራፍ ውድድሩን በምስራቂቷ የሀገሪቱ ክፍል (ድሬዳዋ) ማከናወን ጀምሯል። በሀገራችን እጅግ እየተንሰራፋ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስን በመከላከል በበርካታ ገደቦች ታጅቦ እየተደረገ የሚገኘው ሊጉም በድሬዳዋ ፈታኝ ነገሮች ከፊቱ እየተጋረጡበት ይገኛል። በዚህም በርካታ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን በቫይረሱ ምክንያት ከጨዋታዎች እያጡ ይገኛሉ።

ይህንን ተከትሎም የሊጉ የበላይ አካል አክሲዮን ማኅበሩ ከደቂቃዎች በኋላ የሁሉንም ክለብ የቡድን መሪዎች ለምክክር እና የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለማስተላለፍ መጥራቱ ታውቋል። በዚህ ስብሰባ ላይም የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙ እና ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ከቫይረሱ ሊጠብቁ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ተገልጿል።


© ሶከር ኢትዮጵያ