ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ ያገኘበትን ውጤት አስመዝግቧል

የወራጅነት ስጋት ያለባቸው ጅማ እና ድሬዳዋ ያደረጉት ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመሩት ጅማ አባጅፋሮች በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ ሦስት ተጫዋቾች ለውጠዋል። በዚህም መላኩ ወልዴ፣ አብርሀም ታምራት እና ሳዲቅ ሴቾን በአዲስ ፈራሙዎቹ አሌክስ አሙዙ ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ራሂም ኦስማኖ ተክተዋል። በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ድሬዳዋዎች ደግሞ በ16ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረቱበት ቋሚ ስብስብ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም በያሬድ ዘውድነህ እና ሄኖክ ገምቴሳ ምትክ በረከት ሳሙኤል እና አዲስ ፈራሚው ዳንኤል ኃይሉን ወደ ቋሚነት አምጥተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን ከመጀመራቸው በፊት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ “እኔ የሰላም አምባሳደር ነኝ።” የሚል አጠር ያለ መልዕክት ከተጫዋቾቹ ጋር በመሆን ስታስተላልፍ ተሰምቷል።

በከተማቸው ጨዋታውን የሚያደርጉት ድሬዳዋዎች ኳስን በተሻለ በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር። በተለይም በ5ኛው ደቂቃ ጁንያስ ናንጄቦ በፈጠረው ጥሩ ጥቃት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም የቡድኑን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገው ናንጄቦ ከመዓዘን ተሻምቶ አቡበከር ኑሪ ያወጣውን ኳስ በመጠቀም ሌላ ጥቃት ፈፅሟል። ገና ከጅምሩ ጫናዎች የበዛባቸው ጅማዎች በበኩላቸው የጨዋታውን የመጀመሪያ ደቂቃዎች መከላከል ላይ ተጠምደው አሳልፈዋል። አዲሱ አጥቂያቸው ራሂም ኦስማኖን ብቻ ፊት ላይ በማድረግም ረጃጅም ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለግብ ማስቆጠሪያነት ሲጠብቁ ተስተውሏል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት ድሬዳዋዎች በ19ኛው ደቂቃ ተጋጣሚያቸውን ያስደነገጡበት ሌላ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። በዚህ ደቂቃም ናንጄቦ በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን እየገፋ የገባውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ኢታሙና ኬይሙኒ አቀብሎት ኢታሙና ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ኢታሙና በ42ኛው ደቂቃ ደግሞ ራሱ ላይ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ ኳሱን በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር። አጋማሹ ተጠናቆ የዕለቱ ዳኛ የጨመሩት ደቂቃ ሲጀመር አጋማሹን በመከላከል ያሳለፉት ጅማዎች እጅግ ለግብነት የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። በዚህም የመስመር ተከላካዩ ኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በአግባቡ ሳይቆጣጠረው ዋለልኝ አግኝቶት ጥሩ ሙከራ ተፈፅሟል። ይሁን እና የድሬዳዋ ከተላካዮች በቶሎ በመድረስ ዋለልኝ ዕድሉን እንዳይጠቀምበት አድርገውታል። በአጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ሻል ብለው የቀረቡት ጅማዎች በ56ኛው ደቂቃ በተፈጠረ አጋጣሚ የድሬዳዋን ግብ ጎብኝተዋል። በዚህም ተመስገን ደረሰ የተላከለትን ረጅም ኳስ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ቀድሞ ለማግኘት ጥሮ የግብ ዕድል ለመፍጠር ታትሮ ነበር። በጨዋታው የወሰዱትን ብልጫ በጎሎች ማጀብ ያልቻሉት ድሬዳዋዎች ደግሞ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከግራ መስመር ተሻምቶ ናንጄቦ በሞከረው ኳስ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ በእነሱ በኩል አድርገዋል። በጨዋታው እጅግ ለግብነት የቀረበ ሙከራ የተደረገው ግን በ63ኛው ደቂቃ ነው። በዚህ ደቂቃም ተመስገን ደረሰ ቡድኑ ያገኘውን የቅጣት ምት ፍሬው መረብ ላይ ለማሳረፍ ጥሮ የግቡ ቋሚ መልሶበታል።

ጨዋታው ቀጥሎም በ75ኛው ደቂቃ ጅማዎች ኦስማኖ ተከላካዮች ያፀዱትን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ወደ ግብ በመታው ኳስ ጥቃት ሰንዝረዋል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን በጨዋታው የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋዎች የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በዚህም የመሐል ተከላካዩ ውብሸት በሙኅዲን ሙሳ ላይ በሰራው ጥፋት ቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። በ78ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም አዲሱ የቡድኑ ተጫዋች ዳንኤል ኃይሉ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከጎሉ በኋላም የድሬ ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኝ ዘማርያም አቅንተው ኪሱ ውስጥ ሦስት ነጥቡን የመክተት ምልክት በማሳየት ደስታቸውን ገልፀዋል።

መሪ የሆኑት ድሬዳዋዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ቀርበው ነበር። በዚህም ናንጄቦ በመልሶ ማጥቃት ከተከላካይ ጀርባ አምልጦ ያገኘውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ራሱን ለጎል አመቻችቶ ቢመታውም የግቡ ቋሚ መልሶበታል። በድጋሜ በ94ኛው ደቂቃ ተመሳሳይ ዕድል ያገኘው ናንጄቦ በግራ እግሩ የመታው ኳስ በድጋሜ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ድሬዎች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ጥንቃቄን መርጠው ሲንቀሳቀሱ ሲታይ ጅማዎች ደግሞ የጎል ዕድሎችን ባይፈጥሩም ወደ ተጋጣሚ ተጠግተው ለመጫወት ሞክረዋል። የጨዋታው መገባደጃ ደርሶም በከተማቸው የተጫወቱት ድሬዳዋዎች ከስድስት ጨዋታ በኋላ ድል ያደረጉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ያገኙት ድሬዳዋዎች ነጥባቸውን 16 በማድረስ (10ኛ ደረጃ) በተወሰነ መልኩ ከወራጅ ቀጠናው ራቅ ብለዋል። በፍፁም ቅጣት ምት ግብ የተረቱት እና በጨዋታው ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ጅማዎች ደግሞ በ16 ጨዋታ ባገኙት 10 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ