የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 0-1 ድሬዳዋ ከተማ

በድሬዳዋ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ከአሠልጣኞቹ ተቀብሏል።

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ጅማዎች በተመስገን አማካኝነት ስለሞከሩት ኳስ እና አጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ?

ተመስገን ጥሩ ኳስ ነበር የሞከረው። እኛም የተቆጠረ ነበር የመሰለን። በአጠቃላይ ጨዋታውን ካየነው ግን የግቦቹ ቋሚ እና አግዳሚዎችም ከእነሱ ጋር ነበሩ። በተደጋጋሚ የግቡ አንግሎች ኳሶቻችንን ይመልሱ ነበር። በአጠቃላይ የተሻለው ቡድን ሦስት ነጥብ ከጨዋታው ይዞ ወጥቷል።

ስለ ፍፁም ቅጣት ምቱ?

ተገቢ የፍፁም ቅጣት ምት ነው ዳኛው የሰጠን። ምክንያቱም ተጫዋቻችን ኳስ እየገፋ እያለ ነው የጠለፉት። ስለዚህ ፍፁም ቅጣት ምቱ ተገቢ ነው።

ግቡ ከተቆጠረ በኋላ ስለነበረው የደስታ አገላለፅ?

ተጫዋቾቼ ግቡ ከተቆጠረ በኋላ ኪስህ ውስጥ ሦስት ነጥብ ከተንልሃል እያሉኝ ነበር። ሁላችንም ደግሞ በጣም ደስ ብሎን ነበር።

ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረገው የእንቅስቃሴ ለውጥ?

ዛሬ ከወትሮ በተለይ ኳስን ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። ይህንን ስናደርግ ደግሞ ከጎሉ ራቅን። ከዚህም መነሻነት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ በሁለተኛው አጋማሽ ተነጋግረን ወደ ሜዳ ገብተናል። በተነጋገርነውም መሠረት ስኬታማ ሆነናል። በዚህም ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን ጎል አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ?
የዛሬው ጨዋታ ለሁለታችንም ቡድኖች ወሳኝ ነበር። እኛም የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሳናደርግ እና አዳዲሶቹን ተጫዋቾች ከነባሮቹ ጋር ሳናዋህድ ለዛሬው ጨዋታ የቀረብነው። በዚህም ትንሽ የመዋሀድ ችግር ነበረብን። በመጀመሪያው አጋማሽ ቀድመው ጎል እንዳያስቆጥሩብን ጥንቃቄ ስናደርግ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ተጭነን ተጫውተናል። የተጫዋቾች ለውጦችን አድርገን ኳስ ለመያዝም ሞክረናል። ግን በጨዋታው ፍትሀዊ ነገር ሳናገኝ ወጥተናል። ያለን አማራጭም የነበረውን ነገር በፀጋ ተቀብለን ለቀጣይ ጨዋታ መዘጋጀት ነው።

ተመስገን ደረሰ ስላደረገው ሙከራ?

ጥሩ ሙከራ ነበር። በእግር ኳስ የተሞከረ ሁሉ አይገባም እንጂ አጋጣሚው ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። በአጠቃላይ ግን ጨዋታው ለሁለታችንም ወሳኝ ስለነበረ አጓጊ እና አስጨናቂ ነበር። ዞሮ ዞሮ ዛሬ አልተሳካለንም። እግር ኳስም በስህተት የተሞላ ስለነበር ሁሉን ነገር በፀጋ ተቀብለናል።

ጫና ውስጥ እየገባህ ነው?

ያለንበት ደረጃ አሳሳቢ ነው። ያም ሆነ ይህ ግን እግር ኳስ ተስፋ የምትቆርጥበት አደለም። ስምንት ጨዋታዎች ይቀሩናል። ዛሬ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው። ከዚህ በኋላ ደግሞ ጠንክረን እና ተስተካክለን እንቀርባለን ብዬ እገምታለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ