የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-2 ፋሲል ከነማ

ከደቂቃዎች በፊት ከተጠናቀቀው የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው?

የጨዋታው የመጨረሻ ሰዓት ላይ የወላይታ ድቻ የተወሰኑ ተጫዋቾች እንደታመሙ ሰምተን ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ሜዳ ላይ የነበረው ነገር ከዚህ የተገላቢጦሽ ነው። ሜዳ ውስጥ የነበሩት የድቻ ተጫዋቾች በጣም ጥሩ ነበሩ። ማድረግ የሚፈልጉትን ነገር ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነትም ደስ ይላል። እኛ ደግሞ የዛሬውን ጨዋታ እንደ ፍፃሜ ነበር የወሰድነው። ምክንያቱም ከተከታዮቻችን የምንርቅበት ዕድል ያለን ዛሬ ነበር። በዚህም ስሌት በሁለቱም አጋማሽ የነበረን ነገር ጥሩ ነው። በተወሰነ መልኩ የሚቆራረጡ ነገሮች ቢኖሩትም አጠቃላይ የቡድናችን አደረጃጀት ጥሩ ነበር። ያገኘነውም ውጤት እጅግ አስደስቶኛል። ለቀጣይ ጨዋታዎችም የሚያነሳሳን ይሆናል። ከዚህም በኋላ በድሬዳዋ በሚኖሩን ጨዋታዎችም ትልቅ ስንቅ ለሀዋሳው ውድድር ይዘን የምንሄድ ይመስለኛል።

ስለወላይታ ድቻ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ?

የእኛ ቡድን ኳስ ተቆጣጥሮ ይጫወታል። የኳስ ቁጥጥራችንንም ደግሞ ተቃራኒ ሜዳ ላይ ነው ለማድረግ የምንሞክረው። ግን የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ኳስ መስርተን እንዳንወጣ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት እጅግ የሚደነቅ ነው። በፍፁም የጎደሉ አይመስሉም ነበር። በዚህ አጋጣሚም የዛሬውን ቡድን ላመሰግነው እፈልጋለሁ። በአጠቃላይ ጨዋታው ትንሽ ፈተና ቢኖረውም የእኛ ተጫዋቾች በአሸናፊነት ጨርሰውታል።

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ሰባት ወሳኝ ተጫዋቾችን በህመም ምክንያት አጥቶ ስላደረገው ጨዋታ?

ሰባት ወሳኝ ተጫዋቾችን በአንድ ጊዜ ማጣት ያስደነግጣል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ያልታሰበ ነገር ይዘው ይመጣሉ። ካልተጠበቁ ተጫዋቾች የማይጠበቅ ነገር እንደሚመጣም ማሳያ ነው። በእርግጥ ጨዋታውን ተሸንፈናል ግን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ የግብ ማግባት ዕድሎችን ስንፈጥር ነበር። ግን የመጠቀም ችግር ነበረብን። በአጠቃላይ ግን በዛሬው የተጫዋቾቼ ብቃት ተደስቻለሁ። ረክቻለሁ!

ወደ ሜዳ ይዞት ስለገባው አጨዋወት?

ጥንቃቄ አልመረጥንም። እኛ በመጀመሪያ አስበነው የነበረው የእነሱን የመስመር አጨዋወት ማቆም ነበር። በተለይ ክሮስ እንዳያደርጉ ተነጋግረን ነበር። በተቃራኒው ይህንን የመስመር አጨዋወት አቁመን መሐል ለመሐል ለማጥቃት ነበር ያሰብነው። ከዚህ መነሻነት የመስመሩን ቦታ ስንዘጋባቸው በመሐል ሜዳ ላይ የለውን ሂደት በቁጥር ብልጫ ወሰዱብን። ይህ ደግሞ የእኛን ተጫዋቾች እቅስቃሴ ቀንሶታል። እርግጥ ይህ ከልምድ ጋር የሚመጣ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ