ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

ነገ አመሻሽ 10 ሰዓት የሚደረገውን የ17ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ ከስምንት ጨዋታዎች በፊት ሽንፈት ያስተናገዱት (በ7ኛ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 2-1) ባህር ዳር ከተማዎች አራተኛ ተከታታይ ድላቸውን ድሬ ላይ ለማስመዝገብ ሦስት ነጥብን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሊጉ ወጥ ብቃት ማሳየት የተሳናቸው ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ቁጥር ወደ ሦስት ለማሳደግ እና በዛሬው ዕለት የተሸነፈው ወላይታ ድቻን ደረጃ ለመያዝ ጠንክረው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል።

በመቀመጫ ከተማቸው ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን በማሸነት ጥሩ ተነሳሽነት ላይ የተገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በከተማቸው የተደረገውን የሦስተኛ ምዕራፍ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ካገባደዱ በኋላ ለአንድ ሳምንት ለተጫዋቾቻቸው የእረፍት ጊዜን ሰጥተው ነበር። በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ስብስቡም ከእረፍት በኋላ ዝግጅቱን ሲጀምር በጉልህ የሚታይበትን የአጨራረስ ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ እንደነበር ተገልጿል። እርግጥ አንድ ተጫዋች ብቻ (ፍፁም ዓለሙ) ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ የላከው ቡድኑም ፊት አካባቢ የሚታዩበትን ችግሮች ለመቅረፍ ከመሞከሩ በተጨማሪ የህብረት አጨዋወቶች ላይም ልምምዶችን ሲሰራ መክረሙ ተነግሯል።

ማክሰኞ ምሽት ከባህር ዳር ወደ ድሬዳዋ የተጓዘው ስብስቡ ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾችን በነገው ጨዋታ አለማሰለፉ እንዳያሳሳው አስግቷል። በነገው ጨዋታ ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጡት ተጫዋቾች ሀሪስተን ሄሱ፣ ፍፁም ዓለሙ እና ወሰኑ ዓሊ ናቸው። በሦስቱ ወሳኝ የሜዳ ክፍሎች ከሚጫወቱት ተጫዋቾች በተጨማሪም አቤል ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋች መሆኑ ተሰምቷል። ያም ሆኖ ሌሎቹ ፈጣን ተጫዋቾች ለውሃ ሰማያዊው መለያ ለባሹ ቡድን በጎ ነገሮችን ለማምጣት እንደሚታትሩ ይታሰባል።

በአሠልጣኝ ደጋረገ ይግዛው የሚመራው ወልቂጤ ከተማም በሁለት ከተማ ለሚደረገው ቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጅቱን ማድረግ ከጀመረ ሁለት ሳምንት አስቆጥሯል። ቡድኑም ተጫዋቾቹን ከእረፍት እንደሰበሰበ ወዲያው ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ለ14 ቀናት ልምምዱን ሲሰራ ቆይቷል። ከፍተኛ የጎል ማስቆጠር ችግር ያለበት ቡድኑ በ14 ቀናት የዝግጅት ቆይታው እንደ ባህር ዳር ሁሉ ማጥቃቱ እና ግብ ማስቆጠሩ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ እንደነበር ታውቋል።

ሞቃታማዋን ከተማ ለመልመድ ከ14 ቀናት በፊት ድሬን የረገጠው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው ባህር ዳር የተሻለ የአየር ሁኔታውን መልመዱ ጥሩ ነገር እንደሚሰጠው ይገመታል። በተጨማሪም ግብ ላይ አይናፋር የሆነው ቡድኑ እስራኤል እሸቱን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ የፊት መስመሩም ሊያስልለት ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን በየጨዋታው በአማካይ ከአንድ በላይ ጎሎችን የሚያስተናግደው የቡድኑ የኋላ መስመር ፈጣኖቹን የባህር ዳር ተከላካዮች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ብቃት ላይ መገኘት የሚኖርበት ይመስላል። በሠራተኞቹ በኩል አሳሪ አልመሀዲ ጉዳት ላይ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ተነግሯል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በፕሪምየር ሊጉ የትመዘገበ የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን በመጀመሪያው ዙር ሲያደርጉ ወልቂጤ ከተማ በቶማስ ስምረቱ ብቸኛ ግብ ባለድል መሆን ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሰለሞን ወዴሳ – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ

አፈወርቅ ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ሳምሶን ጥላሁን

ዜናው ፈረደ – ባዬ ገዛኸኝ – ግርማ ዲሳሳ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሤ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – አብዱልከሪም ወርቁ

ሄኖክ አየለ – እስራኤል እሸቱ – ያሬድ ታደሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ