የ17ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።
የኮቪድ ወረርሺኝ ጥላ ያጠላበት ይህ ጨዋታ ሁለት ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉ ቡድኖችን ያገናኛል። ከውጤት አንፃር በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ከመገኘታቸው ባለፈ አዳዲስ አሰልጣኞችን አምጥተው እና ተጫዋቾችን አስፈርመው ከመውረድ ለመትረፍ እያደረጉት ያለው ጥረትም ሲዳማ እና አዳማን ያመሳስላቸዋል።
በባህር ዳሩ ውድድር አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን የተጠቀመው ሲዳማ ቡና ቤኒናዊውን ግብጠባቂ ፋቢያን ፋርኖሌንም ወደ ስብስቡ አካቷል። አምስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገኙት ሲዳማ ከበላዩ ያለው ድሬዳዋ ከተማ ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነታቸው ወደ አምስት ከፍ በማለቱ የነገው ጨዋታ በእጅጉ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይ 10ኛው ሳምንት ላይ ሀዋሳን ከረታ በኋላ አንድም ነጥብ ያላገኘው አዳማ ስድስት የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን በእጁ አስገብቶ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አምስት የውጪ ተጫዋቾችን ጨምሮ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። ሴኩምባ ካማራሚ ፣ ማማዱ ኩሊባሊ ፣ ላሚኔ ኮማሬ ፣ ላውረንስም ኤድዋርድስ እና ኤሊሴ ዲማንኬልን ያስፈረመው አዳማ ከሊጉ ግርጌ ተለቆ ቢያንስ የጅማ አባ ጅፋርን ቦታ ለመያዝ የነገውን ፍልሚያ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
ዛሬ ላይ እየተሰሙ ባሉ መረጃዎች በርከት ያሉ የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በኮቪድ 19 መጠቃታቸው መረጋገጡ እየተናፈሰ ይገኛል። በተለይም የሲዳማ ቡድን አባላት እጅግ ከፍ ባለ ቁጥር በቫይረሱ መያዛቸው በስፋት እየተነገረ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ በሁለቱም ክለቦች በኩል ያለውን ሁኔታ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች 19 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሲዳማ 7 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አዳማ 5 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– 30 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ ግንኙነት ሲዳማ 14 ሲያስቆጥር አዳማ 16 አስቆጥሯል።
* በተጋጣሚዎቹ ዘንድ ተፈጥሯል ስለተባለው ከፍ ያለ የኮቪድ ተጠቂዎች ቁጥር ጥርት ያለ መረጃ ባለማግኘታችን ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አለመቻላችንን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ