አንደኛ ሊግ | ወደ ማጠቃለያ ውድድር የገቡ ቡድኖች ተለይተዋል

ከታኅሳስ 25 ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች ሲደረግ የቆየው የ2013 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት የተጠናቀቁ ሲሆን ወደ ማጠቃለያ ውድድር ያለፉ አስራ ስድስት ቡድኖችም ታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነውና በሦስተኛ የሊግ እርከን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ በምድብ አምስት ከትግራይ ክልል ክለቦች ውጪ በድምሩ አርባ አምስት ክለቦች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ውድድሩ ከኮቪድ 19 ጉዳይ ጋር በተገናኘ በተመረጡ ከተሞች ፕሮቶኮሉን በጠበቀ መልኩ ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከጥንቃቄ አንፃር ከፍተኛ ጉድለቶች ነበሩበት ተብሏል፡፡ ከሌሎች ውድድሮች አንፃር ይህ ውድድር ክፍተቶች እንደነበሩበትም ሶከር ኢትዮጵያ በተገኘችበት ስታዲየም ማስተዋል ችላለች፡፡

በውድድሩ ተካፋይ የነበሩ ክለቦች እንደገለፁት ከኮቪድ ምርመራ ጋር በተገናኘ አድሎአዊ አሰራሮች መኖራቸውን በቅሬታ መልክ የጠቆሙ ሲሆን የሜዳዎች ምቹ አለመሆን፣ ዝቅተኛ ትኩረት፣ ዳኞች ጨዋታን በአግባቡ ያለመምራት፣ በየምድቡ የተመደቡ ሰብሳቢዎች ቅጣት የተላለፈባቸውን ተጫዋቾች ቅጣታቸውን በአግባቡ ሳይተገብሩ በቀጣይ ጨዋታ እንዲሰለፉ መደረጉ የታዩ ችግሮች እንደሆኑ ክለቦች የገለፁ ሲሆን አወዳዳሪው አካል በበኩሉ ክለቦች የኮቪድ 19 ህግን በመተላለፍ በየቦታው መታየታቸው፣ በሜዳ ላይ ክለቦች ለእያንዳንዱ ተጫዋች ውሀን ከማቅረብ ይልቅ አንድ ውሀን ለሁለት እና ለሶስት ሲጠጡ መታየቱ የበሽታው ስርጭት እንዲበዛ ማድረጉ፣ ለተጫዋቾቻቸው ወርሀዊ ደመወዝ ባለመክፈላቸው የፎርፌ ውጤት በተደጋጋሚ መመዝገቡ፣ በቂ የሆነ ሁለተኛ ትጥቅን ክለቦች ማቅረብ ባለመቻላቸው በተዘበራረቀ መለያ ሜዳ ላይ እንዲታዩ መሆኑ እንዲሁም ደግሞ ክለቦች በተያዘላቸው ሰዓት ሜዳ ላይ ለጨዋታ ያለመቅረብ ችግር በስፋት እንደነበር ተገልጿል።

በተለያዩ ከተሞች በተደረጉ ጨዋታዎች አስራ ስድስት ክለቦች በቀጣይ በሚገለፅ ከተማ በሚዘጋጅ የማጠቃለያ ውድድር ማለፍ የቻሉ ሲሆን ምድባቸውን አንደኛ ሆነው የጨረሱ ክለቦች የምድብ አሸናፊ በመሆናቸው የዋንጫ ተሸላሚ ችለዋል።

ከየምድባቸው ለማጠቃለያ ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ያለፉ ቡድኖች

ምድብ 1፡- ኤጄሬ ከተማ፣ ቡራዩ ከተማ፣ አምቦ ከተማ

ምድብ 2፡- ሐረር ከተማ፣ ሞጆ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፓሊስ

ምድብ 3፡- አውሥኮድ፣ እንጅባራ ከተማ እና ጎጃም ደብረማርቆስ፣ ዳሞት ከተማ

ምድብ 4:- ሰንዳፋ በኬ፣ ጉለሌ ክፍለከተማ፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ

ምድብ 6፡- ሾኔ ከተማ፣ ጎባ ከተማ፣ ጎፋ ባራንቼ

በቀጣይ በሚደረገው የሜጠቃለያ ውድድር ስድስት ቀዳሚ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ቡድኖች ወደ 2014 ከፍተኛ ሊግ ያድጋሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ