ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የ18ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታን የተመለከቱ ጉዳዮችን በዳሰሳችን ተመልክተናል።

በድሬዳዋ ውድድር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸው ግብ ካላስቆጠሩ ቡድኖች መሀል የሚጠቀሱት ሰበታ እና ቡና በከተማዋ የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ለማሳካት ይገናኛሉ። ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዲጂት የተሻገረበት ኢትዮጵያ ቡና ይህንን ክፍተት ለማጥበብ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቦታውንም ለማጠናከር ነጥቦቹ ያስፈልጉታል። ሰበታ ከተማዎችም የነጥብ ጥግግት እየታየበት ወዳለው የታችኛው ፉክክር አብዝተው ላለመጠጋት ከነገው ጨዋታ ውጤት ይጠብቃሉ።

ከቡድኖቹ ተመሳሳይ የአጨዋወት ምርጫ አንፃር ክፍት እንቅስቃሴ እንደሚደረግበት የሚጠበቀው ጨዋታ ከፍ ያለ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ እንደሚደረግበት ይጠበቃል። በሀዋሳው ጨዋታ ተጋጣሚውን ማስከፈት እጅግ ከብዶት የዋለው ኢትዮጵያ ቡና ነገ እንደቀድሙት ጨዋታዎች በርከት ያሉ ተሰላፊዎቹን በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ማስገባት የሚችልባቸው ቅፅበቶች ሊፈጠሩለት እንደሚችሉ ይታመናል። ቡድኑ ክፍተት ባላቸው ጨዋታዎች ላይ እንደሚያደርገው ከማጥቃት አማካዮቹ ከሚነሱ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ዕድሎችን መፍጠር ዋነኛው የማጥቃት መንገዱ መሆኑ አይቀርም። በግራ በአስራት ቱንጆ ቀጥተኛ ሩጫዋች እንዲሁም ከቀኝ የሚኪያስ መኮንን የቴክኒክ ብቃት በመታገዝም የሰበታን የኋላ ክፍል ጫና ውስጥ ለመክተት እንደሚሞክር ይጠበቃል።

ሰበታ ከተማ በቅርብ ጨዋታዎች የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ ኳስ መስርቶ የመውጣት ብቃት መሻሻል እና ዳዊት እስጢፋኖስ ቅርባቸው ሆኖ እንዲጫወት የማድረጉ ነገር በተለይም ለእንደ ነገው ዓይነት ጨዋታ የሚጠቅመው ነጥብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከወገብ በላይ ያለው የቡድኑ የኳስ ፍሰት ፈጠን ማለቱም ከቡና የመከላከል ሽግግር በፈጠነ ሁኔታ ወደ አደጋ ክልል እንዲደርስ ሊረዳው ይቻላል። ሰበታ ፊት መስመር ላይ ኦሴይ ማወሊን ማግኘቱ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ብቻ በጎ ፍንጭ መስጠቱ ደካማ የነበረው የቀኝ መስመር ማጥቃቱን የሚያነቃቃላትም ነው። ግዙፉ አጥቂ የአስራት ቱንጆን የማጥቃት ተሳትፎ ተከትሎ ክፍተቶችን ካገኘም አደገኛ ሊሆን ይችላል።

የተሻለውን የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለማግኘት ከባድ ፍልሚያ እንደሚደረግ በሚጠበቅበት በነገው ጨዋታ ግቦች በሁለቱም በኩል የመቆጠር ዕድላቸው ሰፊ ነው። ቢያንስ ክፍተት እና ጊዜ የሚሰጡ ዕድሎች በርከት ብለው ሊገኙ መቻላቸው የሁለቱንም አጥቂዎች የአጨራረስ ብቃት እንድናይ ዕድለን ሊሰጠን ይቻላል።

በሊጉ ያለው ያልጠራ የኮቪድ ሁኔታ ምን ያህል ተጫዋቾች ላይኖሩ እንደሚችሉ ለማወቅ ፈተና ቢሆንም ከጉዳት ጋር በተያያዘ ኃይሌ ገብረትንሳይ በኢትዮጵያ ቡና ታደለ መንገሻ ደግሞ በሰበታ ከተማ በኩል ለጨዋታው እንደማይደርሱ ማወቅ ችለናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በእስካሁኑ የሊግ ግንኙነቶች መመጣጠን ከሚታይባቸው ተጋጣሚዎች ውስጥ ቡና እና ሰበታ ተጠቃሽ ናቸው። ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ጊዜ ድልን ማጣጣም ሲችሉ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ላይ ነጥብ ተጋርተዋል። በሰባቱ ግጥሚያዎች ሁለቱም ሰባት ሰባት ግቦችን ማስቆጠራቸውም ለተመጣጣኝ ፉክክራቸው ሌላው ማሳያ ነው።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ