ከፍተኛ ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ የፕሪምየር ሊግ መግቢያ በር ላይ ደርሷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 17ኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በእጅጉ ያቃረበውን ድል አስመዝግቧል።

ዛሬ አስር ሰዓት ላይ ሀላባ ከተማን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ 3-0 ማሸነፍ ችሏል። ፍፁም ጥላሁን በ16ኛው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ ሲያደርግ ዘርዓይ ገብረሥላሴ በ21ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ብዙዓየሁ ሰይፈ የማሳረጊያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ድሉን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ከ17 ጨዋታ 44 ነጥቦች መሰብሰብ ሲችል ተከታዩ ሀምበሪቾ በዚህ ሳምንት መሸነፉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ 13 ከፍ አድርጎ መሪነቱን ያጠናከረ ሲሆን በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ሶዶ ከተማን ካሸነፈ ሦስት ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከአምስት ዓመታት በኋላ መመለሱን ያረጋግጣል።

በ2004 የተመሰረተውና በቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ኮከብ እስማኤል አቡበከር የሚሰለጥነው አዲስ አበባ ከተማ በ2009 ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ በዛው ዓመት ከሊጉ መውረዱ የሚታወስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ